‹‹ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን ምንነት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡›› ወጣቶች

228

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 20/2012ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ወጣቶች ማኅበር 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን በባሕር ዳር እያካሄደ ነው፡፡ በጉባኤው የየክልላቸውን ወጣት ማኅበራት ወክለው የመጡ ወጣቶች ከአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ሊቀ-መንበር አዱኛ አሰፋ ‹‹በኢትዮጵያ ባለፈው ሥርዓት ከተሠራው አስከፊ ትርክት አንጻር ሲታይ ወጣቱ ጥሩ ደረጃ ላይ አለ ማለት ይቻላል›› ነው ያለው፡፡ አሁን ላይ የሚታየውን አለመግባባት ሥርዓቱ የወለደው እንደሆነም ነው የገለጸው፡፡

‹‹ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን ምንነት ማወቅ ያስፈልጋል›› ያለው አዱኛ ወደ አንድ ለመምጣት ገዢ መደብንና ሕዝብን መለዬት አስፈላጊ መሆኑን አመላክቷል፡፡ አንድ ገዢ ከአንድ ብሔር ስለወጣ የእኔ ነው ወይንም የእነርሱ ነው ብሎ ማሰብ አደጋ እንዳለውና ገዢ መደብ መጭ እና ሂያጂ ሕዝብ ግን ቀጣይነት ያለውና ዘላቂ እንደሆነም አመላክቷል፡፡ ወጣቱም ብሔርን፣ እምነትንና ሥርዓትን በደንብ ለይቶ ማወቅ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ከዳር እስከ ዳር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተመሳሰይ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የገለጸው አዱኛ አንዱ ጨቋኝ ሌላው ደግሞ ተጨቋኝ አድርጎ የተጻፈው ታሪክ ልክ አይደለም›› ነው ያለው፡፡ ውሸት ሲደጋገም እውነት ስለሚመስል ውሸቱን ማስተካከል ተገቢ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ አንዱ ሌላኛውን እንዳያውቅ ሆኖ የተዘረጋውን ትርክት ማስተካል እንደሚገባ ነው ያስገነዘበው፡፡ ወጣቱ ፖለቲከኞች በሚፈልጉት ቁማር መጫወት እንደማያስፈልግም አቶ አዱኛ ተናግሯል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ለእኔ ምኔ ናቸው?›› ብሎ ማሰብ ተገቢ እንደሆነ ያስገነዘበው ወጣቱ ‹‹እርስ በእርስ አጋርና ውበት መሆናችንን መዘንጋት አይባንም›› ነው ያለው፡፡ አንድ ፖለቲከኛ የጻፈውን ትርክት ይዞ መከትል እንደማያስፈልግና ወጣቱ ታሪክን ማጥራትና ማጥናት እንደሚገባው ነው አዱኛ ያሳሰበው፡፡ ሀገር ሠላም ካልሆነ የመጀመሪያው ተጎጂ ወጣቱ እንደሆነም ያመላከተው አቶ አዱኛ ከዱላ ይልቅ በሐሳብ ማመን እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን ከተወያዬን የሚለያዬን አጀንዳ የለንም›› ብሏል፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትም ለሀገር ሠላም፣ አንድነት ፍቅርና አንድነትን በሚያጎሉ ሥራዎች ላይ መሥራት እንዳለባቸው ነው የተናገረው፡፡ በኢትዮጵያ የተሻለ ሐሳብ የሚያመጣ ፖለቲከኛ የለም ያለው አዱኛ ‹‹በሀገሪቱ ያሉ ፖለቲከኞች ከአሁን ቀደም እንዲህ ተደርጋችኋል እንጂ አሁን ይህን ብንሠራ የተሻለ ሕይወት ይኖረናል አይሉም›› ነው ያለው፡፡ ፖለቲከኖች አካሄዳቸውን ማስተካከል እንዳለባቸውና ወጣቱም የፖለቲከኞች ቅጥረኞችንና የፖለቲካ ነጋዴዎችን መከተል እንደማይገባው ነው ያስገነዘበው፡፡

የትግራይ ክልል ወጣቶች ማኅበርን ወክሎ የመጣው ዳዊት አብርሃ ‹‹የሠላም ግንባታ ሲኖር መጀመሪያ ተጠቃሚ የሚሆነው ወጣቱ ነው፤ ወጣቱ በምክንያት መንቀሳቀስ ይገባዋል›› ብሏል፡፡ የትግራይ ክልል ወጣቶች መልካም ግንዛቤ እንዲኖራቸው እየሠሩ እንደሆነ የገለጸው ዳዊት ወጣቱ በአሉባልታና በስማ በለው መጓዝ እንደሌለበትም አሳስቧል፡፡ ‹‹የአማራና የትግራይ ሕዝቦች የረጅም ዘመን የታሪክ ባለቤቶች እንደሆኑ የገለጸው ዳዊት ሁለቱ ሕዝቦች ከሌላው በተለዬ የተቀራረበ ፍቅር፣ ባህል እና ትስስር ያላቸው ሕዝቦች ናቸው›› ብሏል፡፡ ‹‹የሚያለያዩንን ነገሮች በውይይት መፍታት በፍቅር የሚያስተሳስሩንን ደግሞ እያጎላን መሄድ ይባናል›› ብሏል፡፡ ሁለቱን ሕዝቦች የበለጠ ለማቀራረብም ከአማራ ወጣቶች ጋር የጋራ የምክክር መድረክ ማድረግ እንደሚፈልጉ ነው የገለጸው፡፡ በተለይ የአማራና የትግራይ ወጣቶች የአባቶቻችን ታሪክ ማስቀጠል እንጂ ልዩነታችንን ማስፋት የለብንም ሲልም አስገንዝቧል፡፡ ‹‹ወጣቱ የፖለቲካ መሳሪያ መሆን የለበትም›› ያለው ዳዊት ችግር የፈጠረውን አካል በጋራ መጠዬቅ እንደሚገባ፣ ችግሮቹ የማን እደሆኑና እንዴት? እንደተፈጠሩ እንዴትስ መፍታት ይገባል? ብሎ መወያዬት እንደሚገባም አሳስቧል፡፡ ወጣቱ ‹ሂድ› ሲባል የሚሄድ እና ‹ና› ሲባል የሚመጣ ሳይሆን ‹ለምን?› ብሎ የሚጠይቅ መሆን መቻል እንዳለበትም አስገንዝቧል፡፡

የአማራ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዓባይነህ መላኩ ወጣቶች ነገሮችን ማመዛዘን እንደሚገባቸውና ጥያቄዎችንም በየደረጃው መጠየቅ እንደሚገባቸው ነው የተናገረው፡፡ ችግሮችንም በውይይት መፍታት እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ የክልሉን ወጣት በገጠርና በከተማ ለማደረጃት እየሠሩ እንደሆነ የተናገረው ፕሬዝዳንቱ በአማራ ክልል ከ7 ሚሊዮን በላይ ወጣት እንዳለ ቢገመትም እስካሁን የተደራጀው 1 ሚሊዮን እንደማይሆን ተናግሯል፡፡ ወጣቱ ሕጋዊ መሠረት ይዞ መደራጀት እንደሚገባው ያስገነዘበው ፕሬዝዳንቱ ‹‹በአማራ ወጣቶች የሚነሳው ጥያቄው ተመሳሳይ ስለሆነ በጋራ መሥራት ይገባል›› ነው ያለው፡፡ ማኅበሩ ከተመሠረተበት 1995ዓ.ም ጀምሮ የራሱን አስተዋጽዖ ማድረጉንና ነገር ግን በሚገባው ልክ ደግሞ አለመሥራቱን አመላክቷል፡፡ ‹‹መንግሥትም ለማንኛውም አደረጃጄት ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻል አለበት፤ ሁሉንም አደረጃጀት በእኩል ዓይን ማዬት አለበት›› ነው ያለው፡፡

ከዚህ በፊት መንግሥትን የሚታገል ማኅበር አልነበረም›› ያለው ፕሬዝዳንቱ በዚህ ወቅት በጋራ ሆኖ መንግሥትን መታገል እንደሚገባ አመላክቷል፡፡ በክልሉና ከክልሉ ውጭ የሚኖረውን የአማራ ወጣት ጠንካራ የሆነ አደረጃጀት በመፍጠር በሀገሪቱ ያለውን ፀጋ እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረው የአማራ ወጣቶች ማኅበር የክልሉን ወጣቶች አብሮ እንሥራ እያለ እንደሆነና ከሌላው ወጣት የተለዬ ዓላማና ጥያቄ እንደሌለም ነው ያስታወቀው፡፡

ዘጋቆ፡- ታርቆ ክንዴ

Previous articleበሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ሦስት ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት ቃል ገቡ።
Next article‹አረንጓዴው ዘብ› እየተፈተነ ነው፡፡