“ሰሞኑን ተከስቶ ከነበረው ችግር በመውጣት ወደ መደበኛ ሥራችን ተመልሰናል” የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ አርሶ አደሮች

59

ባሕር ዳር: ነሐሴ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር በሌ ዳኛው የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ተዘባ ገንበራ ቀበሌ አሥተዳዳሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር በሌ በአካባቢው አላስፈላጊ ብጥብጥ በመከሰቱ የአካባቢው ወጣቶች ለህልፈት ተዳርገዋል ነው ያሉት፡፡

አካባቢው ሰላም ባለመቆየቱ የመኸር ሰብሎችን ማረም፣ መኮትኮት፣ ማዳበሪያ መጨመር አለመቻላቸውን ይናገራሉ፡፡

አሁን ሁሉም አርሶ አደር ወደ ሥራው ተመልሷል ያሉት አርሶ አደር በሌ በሰላም እጦት ምክንያት ማዳበሪያ ወደ አካባቢው ባለመግባቱ ሰብላቸው የተወሰነ መቀጨጭ እንዳሳዩ ያነሳሉ፡፡

በአካባቢው የተከሰተ ችግር ውድመቶችን ከማስከተሉ በፊት ውይይት እና ንግግር ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የመጣው ማዳበሪያ በፍትሐዊነት ለማከፋፋል እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው የሚሉት አርሶ አደር በሌ ሌሎች አርሶ አደሮችም በንቃት ሥራቸው ላይ እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደር አማረ በላቸው ምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ተዘባ ገንበራ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር አማረ ጊዜው የመኸር እርሻ በበቂ ኹኔታ እንክብካቤ የሚደረግበት ቢኾንም በወረዳው በተከሰተ ሁከት በርካታ ሕጻናት ያለወላጅ፣ አረጋውያን ያለጧሪ እና ቀባሪ ቀርተዋል ይላሉ፡፡

አርሶ አደር አማረ በብጥብጡ ምክንያት ሥራ ቢያቋርጡም አሁን ወደ ሥራ መመለሳቸውን ነው ያነሱት፡፡ ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ ነው፤ ሰላም በሌለበት ምንም ማድረግ አይቻልም ለሰላም ሁሉም ዘብ ልንቆም ይገባል ብለዋል፡፡

ማዳበሪያ ዘግይቶ በመምጣቱ ዘግይቶ የተዘራው ሰብል በቂ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ገልጸው በተቻላቸው አቅም እንክብካቤ እያደረጉ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

አርሶ አደር አማረ የአካባቢው ማኅበረሰብ በተፈጠረው ችግር የወደሙ ንብረቶችና የጠፋውን የሰው ሕይወት መተካት ባይቻልም ቀሪውን በመረዳዳት እና በመተጋገዝ ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የአካባቢዉን ሰላም ለመጠበቅ ሁሉም በጋራ ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባም አርሶ አደር አማረ አሳስበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበፀጥታ አለመረጋጋቶቸ ምክንያት ዕቅዱን ተከትሎ ሥራዎቹን ለማከናወን መቸገሩን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለጸ፡፡
Next articleበትራንስፖርት ችግር ምክንያት ነፍሰጡር እናቶች እና አቅመ ደካሞች ጉዳት ደርሶባቸዋል” የባጃጅ አሽከርካሪዎች