በፀጥታ አለመረጋጋቶቸ ምክንያት ዕቅዱን ተከትሎ ሥራዎቹን ለማከናወን መቸገሩን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

31

ባሕር ዳር: ነሃሴ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ተግባራት ለምክር ቤቱ አቅርቧል።

ኮሚሽኑ ሀገራዊ አጀንዳዎችን እና የምክክሩን ተሳታፊዎች የመለየት ሥራ አጠናክሮ መቀጠሉ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን አጀንዳዎችና የምክክሩን ተሳታፊዎች የመለየት ሥራ አጠናክሮ መቀጠሉን የገለጸው ኮሚሽኑ በ2015 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ሥራዎች በተመለከተ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርቧል፡፡
ኮሚሽኑ እስከአሁን በአምስት ክልሎች የሀገራዊ አጀንዳዎች እና የምክክሩን ተሳታፊዎች የመለየት ሥራ አከናውኗል።

የመጀመሪያ ዙር ሥራውን በማጠናቀቅ ከመጀመሪያ ዙር ያገኛቸውን ልምዶች መነሻ በማድረግ በሌሎች ክልሎች በቀጣይ ዙር የአጀንዳና የምክክሩ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ እንደሚሠራ አስታወቋል፡፡

ቀጥሎም ሁሉን ባሳተፈ ሁኔታ በውይይትና ምክክር ወደ ተግባር ምዕራፍ ለመግባት ዝግጅት እያደረገ መኾኑን አስታውቋል፡፡ እስከአሁን በሀገር ደረጃ የሚያወዛግቡንን ጉዳዮች በመለየትና በመወያየት እንደ ሀገር ከግጭትና ቀውስ አዙሪት ውስጥ ለመውጣት እንዲቻል በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የተጣለበትን ታላቅ ኀላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ መኾኑንም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ እየሠራቸው ያሉትን በርካታ ሥራዎች በተሠጠው ሀገራዊ ተልዕኮ መሠረት በማድረግ ሥራዎቹን ለሕዝብ በሚዲያ ተደራሽ ለማድረግ አደረጃጀቱን ሊያጠናክር እንደሚገባ ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ አካታች፣ አሳታፊ እና ገለልተኛ ኾኖ ምክክሩን በፍጥነት በመጀመር ሀገራዊ ግቡን እንዲመታ የኮሚሽኑ አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ በርትተው እንዲሠሩ ምክትል አፈ-ጉባኤዋ አሳስበው የኮሚሽኑ ሥራዎች በሚዲያ ተደራሽ ኾነው ምክክሩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያማከለ እንዲኾን ምክር ቤቱ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ፤ ኮሚሸኑ በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸውን ሥራዎች አድንቀው፤ ተቋማዊ አሠራሮችን ማዕከል በማድረግ እና ሁሉንም የሚዲያ አማራጮች በመጠቀም የምክክር ኮሚሽኑ ሁሉን የሚያሳትፍ መኾን ይገባል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሕዝብ የጣለበትን ተልዕኮ በሚገባ ግቡን እንዲመታ ለማስቻል በሚዲያ ባለሙያዎች የታገዘ መኾን እንዳለበት አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ተቋማዊ በኾነ መንገድ ሚዲያን ተጠቅሞ የኮሚሽኑን አዋጅ፣ ስትራቴጅዎች ፣ አፈጻጸሞች እና መልዕክቶች ለሕዝቡ ለማስተዋወቅ አቅዶ መንቀሳቀስ እንዳለበት አስገንዝበው፤ ለተግባራዊነቱም መንግሥት እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስቴሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በቀረበው ዓመታዊ ሪፖርት አጅግ አበረታች ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ መረዳታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በሚዲያና የኮሚዩኒኬሽን ሥራዎች የመወያያ አጀንዳዎችን በመለየት ከተለያዩ የኅብረተስብ ክፍሎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለማወያየት መቻሉ አበረታች መኾኑን መረዳታቸውን ገለጸዋል፡፡ በቀጣይም የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራዎችን በፍጥነት መሥራት እንደሚገባና በተያዘው የግዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲተገበር አመላክተዋል፡፡ በዚህም እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ አጀንዳ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ የትኩረት መስኮችን በመለየት የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራውን በተገቢው ሁኔታ ለመፈጸም የሚያስችሉትን ሥራዎች እየሠራ መኾኑን የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን ዓመታዊ የሥራ ክንዉኑን ያቀረቡት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አሳታውቀዋል፡፡

የትኩረት መስኮች ተብለው የተጠቀሱት የላቀ ሀገራዊ ምክክር፣ ስትራቴጂዊ አጋርነት ትስስር፣ የላቀ የሕዝብ ተሳትፎ ማድረግ እንዲቻል የሦስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቀድ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱ፤ ኮሚሽኑ መዋቅራዊ አደረጃጀት አዘጋጅቶ የሰው ኀይል ለማሟላት ጥረት ማድረጉ በጥንካራ ጎን የሚወሰዱ ጉዳዮች ሲኾኑ ኮሚሽኑ ከነበሩ የጸጥታ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ በተፈለገው ፍጥነት ለማከናወን የሚያስቸግሩ ጉዳዮች ቢኖሩም ሀገራዊው የምክክር መድረክን በቀጣይ ለማሰካትና በሀገር አቀፍ ደረጃ በሰፊው ለመሥራት የሚያስችሉ እጅግ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ ተባባሪ አካላትን እና መድረኮች የሚካሔዱባቸውን ቦታዎች የመለየት፣ ለሥልጠና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እንዲሟሉ የማድረግ እንዲሁም ስለምክክር ኮሚሽኑ የአሠራር ሒደት በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር እንዲቻል በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ነገር ግን ከሚዲያና የኮሚዩኒኬሽን ሥራዎች አንጻር ድጋፍ የሚያስፈልግ መኾኑንና የሕዝብና የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አጀንዳ እንዲኾን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ተግባራት ሀገራዊ ፣ ክልላዊና የማኅበረሰብ ሚዲያዎች የሕዝብ ዋነኛ አጅንዳ አድርገው መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡ኮሚሽኑ የስትራቴጂካዊ አጋሮችን የማሰደግ ትስስር ለመሥራት ከበጎ አድርጎት ድርጅቶች፣ ከፖለቲካዊ ድርጅቶች መማክርት፣ የመምህራን ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ ዕድሮች ማኅበርና ሌሎች የሕዝብ ማሳተፊያ የትስስር መንገዶችን በመጠቀም ሁሉንም ተዋንያን ባለድርሻ አካላት አካታች በኾነ መልኩ የምክክር ኮሚሽኑን ሥራ ለማሳከት ሰፊ ሥራ እንደሚሠራም ተመላክቷል፡፡

እስከአሁን በኮሚሽኑ የሕዝባዊ ውይይት በተደረገባቸው ክልሎች ውስጥ በተለያዩ ወረዳዎች የተሳተፉ 51ሺህ 435 ዜጎች መኾናቸውን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ ውይይት በተደረገባቸው ቦታዎች ሕዝቡ በኮሚሽኑ ላይ ትልቅ ተስፋ የጣለ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን የኮሚሽኑን ሥራዎች ተደራሽ ለማድረግ ከተለያዩ ማኅበራዊ እና የግል ሚዲያ ተቋማት እንዲሁም ከክልሎች ሚዲያ ተቋማት ጋር በመነጋገር ዘገባዎች እንዲሠሩ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኮሚሽኑን ሥራዎች ለሕዝቡ ለማስተዋወቅ እና ምክክሩን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ የሚዲያ ተደራሽነት ችግር እንቅፋት እንደኾነባቸው አብራርተው፤ ችግሩን ለመፍታት ምክር ቤቱ እገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሥራውን ለማሳለጥ ከትግራይ ክልል በስተቀር የትውውቅ፣ ተሳታፊዎችን የመለያና የአጀንዳ አሠባሠብ ዘዴ መድረኮች መካሄዳቸውን አብራርተዋል፡፡ የፀጥታ መደፍረስ እና የሎጅስቲክስ መጓተት ኮሚሽኑ ዕቅዱን ተከትሎ ሥራዎቹን እንዳያሳካ ማድረጋቸውን ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበፍኖተ ሰላም ከተማ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
Next article“ሰሞኑን ተከስቶ ከነበረው ችግር በመውጣት ወደ መደበኛ ሥራችን ተመልሰናል” የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ አርሶ አደሮች