
ባሕር ዳር: ነሐሴ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰሞኑ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል፤ ማሕበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል፡፡
ግጭቱ የፈጠረው ምጣኔ ሃብታዊ ጫና ከባድ ከመሆኑ በላይ የደረሰውን ጉዳት እና ውድመት ወደነበረበት ለመመለስ ረጂም ጊዜ ሊወስድ ይችላል ነው የተባለው፡፡
በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ውድመት ከደረሰባቸው ምጣኔ ሃብታዊ ድርጅቶች መካከል አሚናት ሃሚድ የዶሮ እርባታ እና ሥጋ ማቀነባበሪያ ፍብሪካ አንዱ ነው፡፡ ከባሕር ዳር ከተማ የቅርብ ርቀት በወራሚት ቀበሌ ውስጥ የሚገኘው ድርጅቱ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የሃብት ውድመት ደርሶብኛል ብሏል፡፡
የፍብሪካው ተወካይ አቶ ደግአረገ አማረ በተለይም ለአሚኮ እንደገለጹት ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል የተመሰረተው ፍብሪካው ከ66 በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ቋሚ የሥራ እድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡ ከ20 ሺህ በላይ ዶሮዎችን ለማራባት ከተዘጋጁት ሁለት ሸዶች መካከል አንዱ ሙሉ በሙሉ ውድመት ደርሶበታል ነው የተባለው፡፡
የሰላም እጦቱ በባለሃብቱ ብቻ ሳይሆን የሥራ እድል በተፈጠረላቸው ዜጎች ህይዎት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል ያሉት አቶ ደግአደረገ በጠቅላላው ሲታይም ግጭቱ በክልሉ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከባድ እና መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ ጊዜ የሚወስድ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ተወካዩ ገለጻ ፍብሪካው ወደ ሥራ ለመግባት ሙሉ የካፒታል አቅሙን ተጠቅሟል፡፡ አሁን የደረሰበትን ውድመት ተቋቁሞ ወደ ሥራ ለመግባት ብድር እና ሌሎች ድጋፎችን ይሻል ያሉት አቶ ደግአደረገ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል፡፡
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑም መንግሥት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ለሰላም መሥራት እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡ የአካባቢው ማሕበረሰብም መሰል ሕዝባዊ ተቋማትን መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!