ከ35 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ሃብት እንደወደመበት እሸት የግብርና ግብዓት አቅራቢ ድርጅት አስታወቀ፡፡

38

ባሕር ዳር: ነሐሴ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰሞኑ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ተከስቷል፡፡ ከባሕር ዳር ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኘው እሸት የግብርና ግብዓት አቅራቢ ድርጅትም በግጭቱ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ውድመት ደርሶበታል፡፡

እሸት የግብርና ግብዓት አቅራቢ ድርጅት ከተመሰረተ 13 ዓመታትን አስቆጥሯል ያሉን የፕሮጀክቱ ባለሃብት እና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ አድማሱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ እና ግብዓት በማቅረብ በግብርናው ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡

ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ ከ120 ሜትር በላይ ጥልቀት ያለው የከርሰ ምድር ውኃ ቁፋሮ በማካሄድ የአካባቢው ማኅበረሰብ የንጹህ ውኃ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርገናል ብለዋል ሥራ አስኪያጁ፡፡ በፕሮጀክቱ ቅጥር እና የግብርና ግብዓቶች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

እሸት የግብርና ግብዓት አቅራቢ ድርጅት 26 ቋሚ እና ከ50 በላይ ጊዜያዊ ሠራተኞችን የያዘ ሰፊ ድርጅት ነው ያሉት አቶ ዮሐንስ ከሰሞኑ በተፈጠረው ግጭት ሙሉ በሙሉ ውድመት ደርሶበታል ብለዋል፡፡ ግሪን ሃውሶች ፈራርሰዋል፣ ከ1 ሺህ 800 ካሬ በላይ የተዘረጋ የውኃ ማቆሪያ እና የዓሳ ማራቢያ ገንዳም ውድመት ደርሶበታል ተብሏል፡፡

ውድመቱ በገንዘብ ሲተመን ከ35 ሚሊየን ብር በላይ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ ህልውናቸው በድርጅቱ ላይ የተመሰረተው ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው አደጋ ላይ ወድቋል ብለዋል፡፡ የግብርና ግብዓት እንዲቀርብላቸው ጥያቄ ያቀረቡ እና ቀጠሮ የተሰጣቸው አርሶ አደሮችም ማቅረብ አልተቻለም ነው የተባለው፡፡

የደረሰው ውድመት አንድ ጊዜ አልፏል ያሉት አቶ ዮሐንስ እንደገና ከምንም ለመጀመር በመገደዳችን መንግሥት፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ ፕሮጀክቱ ለሕዝብ ተጠቃሚነት እንደመቆሙ ሠራተኞቹን በትኖ ለአደጋ ማጋለጥ አይፈልግም ብለዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰላሙን እስካረጋገጡ ድረስ በቅርብ ሥራ እንደሚጀምርም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል የተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት በክልሉ ልማት እና ኢኮኖሚ ላይ ጫና መፍጠሩን ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር) ተናገሩ።
Next articleግጭቱ በክልሉ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከባድ መኾኑ ተገለጸ፡፡