
ባሕር ዳር: ነሐሴ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አሥተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር) የክልሉን ወቅታዊ ኹኔታ የተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
የተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት በክልሉ ልማት እና ኢኮኖሚ ላይ ጫና መፍጠሩን በመግለጫቸው ተናግረዋል።
ወቅቱ በተለይም የአፈር ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሮች የሚቀርብበት እና የግብርና ሥራዎች በከፍተኛ ትኩረት የሚከናወኑበት ቢኾንም የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱ በዘርፉ ላይ ጫና ፈጥሯል ነው ያሉት።
ባለሀብቶች ለዘመናት ደክመው ያፈሩት ልማት እና ኢንቨስትመንት በተፈጠረው ግጭት መውደሙንም ዶክተር ሰማ ተናግረዋል። ይህ ተግባር ክልሉን በልማት ወደኃላ የሚያስቀር በመኾኑ ሁሉም በጋራ ሊያወግዘው ይገባል ነው ያሉት። የተፈጠረው ግጭት እውነትም የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎችን ለማስመለስ ከኾነ የሕዝቡ ልማቶች መውደም የለባቸውም ነበር ብለዋል።
“አመራር በሰላም ጊዜ ብቻ ሳይኾን በችግር ጊዜም ከሕዝብ ጎን መቆም አለበት” ያሉት ዶክተር ሰማ በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች እና አመራሮች የሕዝብ ሰላም ተጠብቆ ወደ ልማት እንዲገባ በትጋት መሥራት አለባቸው ብለዋል። በርካታ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ስለመኖራቸው ሕዝቡ በየመድረኩ በምሬት እያነሳ መኾኑን መገንዘብ እና ይሄንን ለማስተካከል በቁርጠኝነት መሥራትም ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዶክተር ሰማ “የአማራ ክልል ሕዝብ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ይተማመናል፤ጥልቅ ፍቅርና አክብሮትም አለው” ሲሉም ተናግረዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊትም የአማራ ክልል ሰላም ተመልሶ ሕዝቡም እንዲረጋጋ መስዕዋትነት ጭምር ከፍሏል ነው ያሉት። አሁንም ቢኾን የክልሉ ሕዝብ ለሠራዊቱ ያለውን ክብር ከግምት ውስጥ በማስገባት የክልሉ ሰላም ሙሉ በሙሉ እንዲረጋገጥ መሠራት እንዳለበትም ተናግረዋል።
ሕዝቡ ከሀሰተኛ መረጃዎች እና ውዥንብር ራሱን መጠበቅ እንዳለበትም ዶክተር ሰማ በመግለጫቸው አንስተዋል። ሚዲያዎችም ለሀገር እና ለሕዝብ ህልውና ሲባል ትክክለኛ እና ሚዛናዊ መረጃዎችን ማቅረብ እና ማኅበረሰቡን ከሀሰተኛ መረጃ መጠበቅ አለባቸው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ነጋዴዎች እና ባለሀብቶች የግጭት ጊዜን እንደሰበብ በመቁጠር የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሕዝብን ለተጨማሪ የኑሮ ውድነት ከሚያጋልጥ ተግባር መቆጠብ እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ሕዝቡ እንዲህ አይነት ሥግብግብ ነጋዴዎችን በሚመለከትበት ጊዜ ለሚመለከተው አካል በማመልከት መታገል እንጅ ተባባሪ መኾን እንደሌለበትም ዶክተር ሰማ አሳስበዋል።
ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች አሁን በክልሉ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት እንዲጸና የበኩላቸውን ኀላፊነት እንዲወጡም በመግለጫው ላይ ተነስቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!