
ባሕር ዳር: ነሃሴ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የባጃጅ ትራንስፖርት ክልከላ መነሳቱን ተከትሎ በጎንደር ከተማ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በአማራ ክልል ስድስት ከተሞች አጠቃላይ ሁኔታ ያደረገውን ግምገማ መሠረት በማድረግ ከዛሬ ነሐሴ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ መፍቀዱ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት በጎንደር ከተማ የሚገኙ የባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ከዛሬ ማለዳ 12 ሰዓት ጀምሮ መደበኛ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ክልከላው ከተነሣበት ጊዜ ጀምሮ የባጃጅ ባለቤቶችና አሽካርካሪዎች የጽንፈኛ ቡድኑን አባላት፣ የዘረፉትን ንብረቶችና የትኛውንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ከማጓጓዝ እንዲቆጠቡና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ጥብቅ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።
ይህንን ተላልፈው በተገኙ አካላት ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማዕቀፍ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ መስጠቱም እንዲሁ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!