“የተፈጠረውን ሰላም በማጽናት የአገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማጠናከር እየሠራን ነው” የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ

44

ባሕር ዳር: ነሐሴ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጠረውን ሰላም በማጽናት የአገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማጠናከር እየተሠራ መኾኑን የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ገልጸዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በባሕር ዳር ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት ሠላም የማስከበር ሥራ እያከናወነ ይገኛል። ከተማዋ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋም ተመልሳለች።
በዚህም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በከተማዋ የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴን ጨምሮ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈጠረውን ሰላም ለማጽናት በከተማዋ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል። በዚህም ለሰላም በጋራ ለመሥራት መተማመን ተፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ሰላምን ይበልጥ ማጽናት የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ነው የተናገሩት፡፡

በከተማዋ ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በተለይ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ዝርፊያና ውድመት መከሰቱንም ተናግረዋል። እንደ ኢዜአ ዘገባ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት ደረጃ በደረጃ መልሶ ለማቋቋም እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም በከተማዋ ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን ላይ ዝርዝር ዳሰሳ በማከናወን ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአካባቢያቸውን ሰላም ጠብቀው የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
Next articleበጎንደር ከተማ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ ።