የአካባቢያቸውን ሰላም ጠብቀው የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

43

ባሕር ዳር: ነሃሴ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ነዋሪዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በደሴ ከተማ ተወያይተዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ መሃመድ አሚን በሰጡት አስተያየት፤ በከተማው የልማት ጥያቄያች መልስ እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከአመራሩ ጋር በመቀናጀት በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ በልማት ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ሰሞኑን በነበረው የሰላም እጦት የልማት ሥራዎች በመቋረጣቸው ማዘናቸውን ጠቁመው፤ ሰላም ለሁሉም ነገር ወሳኝ በመሆኑ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሠሩ አስታውቀዋል። የልማትሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ከመንሥት ጎን ተሰልፈን እንሠራለን ብለዋል፡፡

ያለሰላም ወጥቶ መግባትም ሆነ ልማት ማስቀጠል የማይቻል በመሆኑ የአካባቢያቸውን ሰላም በጋራ እንደሚጠብቁ የተናገሩት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ሉባባ ሁሴን ናቸው፡፡

“ባለፈው ጦርነት ከደረሰብን ጉዳት ሳናገግም ሌላ ጦርነት አንፍልግም፣ ሰልችቶናል ያሉት ወይዘሮ ሉባባ፤ ችግሮች ሲከሰቱ በውይይትና በንግግር መፍታት አለብን” ብለዋል፡፡

የተጀመሩ ልማቶች እንዲቀጥሉና እንዳይደናቀፉ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን ለመሥራት ዝግጁ ነን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

“የችግሮች መፍቻ አኩሪ ባህልና እሴቶቻችንን ጠብቀን፣ እርስ በእርስ ተደጋግፈንና ተጋግዘን አንድነታችንን ማስቀጠል አለብን” ያሉት ደግሞ አቶ መስፍን አሸናፊ ናቸው፡፡

ሰላምን በመጠበቅ የተጀመሩ ልማቶችን ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡

ከመንግሥትና ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈው ሰላምንና የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደረገው ጥረትም የድረሻቸውን እንደሚወጡ አመላክተዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ የሀገር መከታ የሆነውን የመከላከያ ሠራዊትን ስም በማጠልሸትና ሰላምን በማወክ ልማትን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ አካላትን በጋራ መታገል አለብን ብለዋል፡፡

ሰሞኑን በተከሰተው ችግር በከፍተኛ ወጪ እየተሠሩ ያሉ የልማት ተግባራት መስተጓጎላቸውን ጠቅሰው፤ ኅብረተሰቡ ሰላሙን በመጠበቅ ልማቱን እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በከተማው ያለውን አንጻራዊ ሰላም በማስቀጠል የኑሮ ውድነቱን፣ እንዲሁም የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በደሴ ከተማ ሁሉም የመንግሥትና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ክፍት ሆነው ኅብረተሰቡን እያገለገሉ መሆናቸውን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል፡፡

የምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል በበኩላቸው፤ ኅብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በጋራ ማስቀጠል ይኖርበታል ብለዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ከውጭ ጠላት ይጠብቃል እንጅ በየሰፈሩ የሚፈጠሩ ችግርን በመፍታት መጠመድም ሆነ ጊዜውን ማጥፋት የለበትም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም እንደየአካባቢያቸው ባህልና እሴት ችግሮችን እየፈቱ የኢትዮጵያን እድገትና ልማት ማፋጠን ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን አለመረጋጋትም በውይይት ጭምር እንዲፈታ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በአጭር ጊዜ ዘላቂ ሰላም ለማምጣትና ልማቱን ለማስቀጠል በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በውይይቱ ላይ የደሴ ከተማ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በከተማችን ንብረት ላይ በዚህ ልክ ጉዳት መድረሱ ያስቆጫል” የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪ
Next article“የተፈጠረውን ሰላም በማጽናት የአገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማጠናከር እየሠራን ነው” የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ