
ባሕር ዳር: ነሐሴ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረማርቆስ ከተማ ላይ በተከሰተው አለመረጋጋት የከተማዋ ንብረቶች ላይ ጉዳት ደርሷል ዝርፊያም ተፈጽሟል።
ይህን ውድመት እና ዝርፊያ ተዘዋውረው የተመለከቱት ነዋሪዎቹ በተፈጠረው ሁኔታ ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ የወደሙ እና የተዘረፉ ተቋማትን ሲመለከቱ ከልብ እንዳዘኑ እና ድጋሜ መደገም የማይኖርበት ተግባር ስለመኾኑ ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡
እያንዳንዱ ማኅበረሰብ የተፈጠረውን የሀብት ውድመት በመመልከት በቀጣይ ሀብቱን እንዲጠብቅ ሥራ መሠራት እንዳለበትም ነው ያብራሩት፡፡
“በከተማችን ንብረት ላይ በዚህ ልክ ጉዳት መድረሱ ያስቆጫል” ያሉት ነዋሪዎቹ ሁሉም ከተፈጠረው ተግባር ሊማር እና ሊጠነቀቅ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በተለይ በአብማ ክፍለ ከተማ የተፈጠረው ውድመት እና ዘረፋ የአንድን ከተማ ልማት ከሚመኝ ዜጋ የማይጠበቅ የእኩይ ሥራ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት፡፡
ወላጆች ልጆቻቸውን መምከር እና ከእንደዚህ አይነት ተግባር እንዲርቁ ማስተማር እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያስረዱት፡፡
የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ሰው ለሰላም እንዲረባረብ እና እንዲህ አይነት ተግባር እንዳይኖር የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆምም ለራሱ ሰላም መሥራት እንደሚጠበቅበትም ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!