
ባሕር ዳር: ነሐሴ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰሞኑን በአማራ ክልል በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ዙሪያ የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ መግለጫ ሠጥቷል፡፡
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አደራጀው ካሴ ከሁከት እና ብጥብጥ የሚገኝ ጥቅም ሳይኾን ሞት እና ንብረት ውድመት በመኾኑ ሁሉም ከዚህ ወጥቶ ለሰላሙ ዘብ ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ክልሉ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ጦርነት ላይ የቆየ እና በርካታ ጉዳት ያስተናገደ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ውድመት ለማገገም እየተሠራ ባለበት በአሁኑ ወቅት እንደዚህ አይነት ግጭት መከሰቱ አክሳሪ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
ለክልሉ ከሚበጀትለት በጀት ውስጥ 65 በመቶ የሚኾነው ከክልሉ ነዋሪዎች የሚሠበሰብ በመኾኑ ክልሉ ራሱን በኢኮኖሚ ለማሳደግ ከግጭት ነጻ መኾን አለበት ብለዋል፡፡
መሥሪያ ቤቱ ገቢ ሰብሳቢ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ በነበረው ሁከት ገቢ ለመሰብሰብ እንቅፋት እንደኾነበት ተናግረዋል፡፡ አቶ አደራጀው ሰላም ከሌለ ገቢ መሰብሰብም ኾነ የተሠበሰበውን ገቢ ለሚፈለገው የሥራ ዘርፍ ማዋል እና የክልሉን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡
ክልሉ ገቢ በወቅቱ እና በሚፈለገው መጠን እንዲሰበስብ እና የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ አካባቢው ከግጭት ነጻ መኾን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ማንኛውም ነዋሪ ሰላሙን ሊጠብቅ እና ሊንከባከበው ይገባል ብለዋል፡፡
ሰላም ከሌለ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ሊጠናቀቁ አይችሉም፡፡ ተጠናቅቀውም ለሕዝብ ጥቅም አይሠጡም፤ ጥቅም እየሠጡ ያሉትም ጉዳት እያጋጠማቸው ነው፤ መልሶ ለመገንባት በርካታ ቢሊዮን ብር የሚጠይቅ እንደኾነም አንስተዋል አቶ አደራጀው፡፡
ካሁን በፊት በነበረው ጦርነት በርካታ ፕሮጀክቶች ተቋርጠዋል፤ አንዳንዶቹ ወድመዋል፡፡ አንዳንድ ወረዳዎች በጦርነቱ ምክንያት ገቢ መሰብሰብ ባለመቻላቸው እስካሁን ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን ያነሱት ምክትል ቢሮ ኀላፊው ይህ እንዳይደገም ሁሉም ለሰላሙ ዘብ ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡
የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ክልሉ ገቢ መሠብሰብ፤ የተሠበሰበውን ገቢ በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እና እድገትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር ሊኾን ይገባል ብለዋል፡፡ በክልሉ በርካታ የመንግሥት ሠራተኞች የሚኖሩበት በመኾኑ የአንድ ወር ደመወዝ መቋረጥ ምን ያህል ቤተሰብን ችግር ውስጥ ሊጥል እና ለጉዳት ሊዳርግ እንደሚችል መረዳት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል ምክትል ቢሮ ኀላፊው፡፡
የመንግስት በጀት ለደመወዝ፣ ለሥራ ማስኬጃ እና ለፕሮጀክቶች የሚውል በመኾኑ ሰላም ከሌለ ደመወዝ መክፈል፣ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንደማይቻልም ግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል ብለዋል፡፡
የክልሉን ኢኮኖሚ ለመለወጥ ሰላም ከሁሉም በላይ አስፈላጊ እና ቅድሚያ የሚሠጠው ጉዳይ መኾኑን ሁሉም ሊረዳው ይገባል ብለዋል፡፡
ተቋማት ሰላማዊ በኾነ መንገድ ሥራቸውን እንዲሠሩ፣ ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ ሰላም አስፈላጊ ነው የሚሉት አቶ አደራጀው በብጥብጥ የሚገኝ ጥቅም አለመኖሩን አንስተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!