
ባሕር ዳር: ነሐሴ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ሰሞኑን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራዎቹን በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ የሁለተኛ ዙር ምዕራፍ ሥራዎችን መጀመሩን ማስታወቁና ክልከላዎችን መጣሉ የሚታወስ ነዉ፡፡
ዛሬ ማለዳ ላይ ባደረገዉ ግምገማ፣የሁለተኛዉ ዙር ወታደራዊ ኦፕሬሽን ሥራዎች ከሞላ ጎደል እየተጠናቀቁና እየተወሰደ ባለዉ ርምጃ አብዛኞቹ አካባቢዎች ወደ መደበኛ ሁኔታ እየተመለሱ መኾናቸዉን አረጋግጧል፡፡
በተፈጠረዉ መረጋጋትና ሰላም፣ በሁሉም አካባቢዎች ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ዉይይት መጀመሩን፣ የመንግሥት፣ የግልና የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ወደ መደበኛ ሥራቸዉ እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን፣ ሕዝቡ ለመከላከያ ሠራዊታችን እያሳየ ያለው አቀባበል፣ የስንቅና የማበረታቻ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ ያለው ፍላጎትና እንቅስቃሴ አበረታች መኾኑን ዕዙ አረጋግጧል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ የፈጠረለትን ሰላማዊ ሁኔታ በመጠቀም አርሶ አደሩ ወደ መኸር አዝመራ ሥራዉ እየተመለሰ ነው፡፡
የግብርና ግብአቶችንም ወደየአካባቢዎቹ ለማጓጓዝ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩን ዕዙ በግምገማዉ አይቷል፡፡
በቀጣዮቹ ቀናት በሚወሰዱ የማጥራት ርምጃዎች የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥብቅ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
የተጀመሩትን መደበኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ ለማጠናከር እንዲቻል፣ ክልከላ በተደረገባቸው ስድስት የአማራ ክልል ከተሞች ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ወይንም በተለምዶ ባጃጅ በመባል የሚጠሩት ተሸከርካሪዎች አገልግሎት እንዲጀምሩ ከኅብረተሰቡ የቀረበዉን ጥያቄ ዕዙ መርምሯል፡፡
ዕዙ በከተሞቹ አጠቃላይ ሁኔታ ያደረገውን ግምገማ መሠረት በማድረግ ከነሐሴ 10 /2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጅ) መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ፈቅዷል፡፡
ከዚህም ጋር በማያያዝ ክልከላዉ ከተነሣበት ጊዜ ጀምሮ የባጃጅ ባለቤቶችና አሽከርካሪዎች የጽንፈኛ ቡድኑን አባላት፣ የዘረፉትን ንብረቶችና የትኛዉንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ከማጓጓዝ እንዲቆጠቡና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ይህንን ተላልፈዉ በተገኙት ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማዕቀፍ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ አዟል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ነሐሴ 9/2015 ዓ.ም አዲስ አበባ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!