
ባሕር ዳር: ነሐሴ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም እጦት የጤና ዘርፉን ሲፈትነው ቆይቷል፡፡ በአማራ ክልል በነበረው የወረራ ጦርነት ትላልቅ ሆስፒታሎችን ጨምሮ በርካታ የጤና ተቋማት ወድመዋል፣ ተዘርፈዋል፡፡ የጤና ተቋማቱ መጎዳታቸውን ተከትሎ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች የጤና አገልግሎት ለማግኘት ተቸግረው ነበር፡፡ የወረራው ጦርነት ካቆመ በኋላ የክልሉ መንግሥት የጤና ተቋማትን መልሶ የማቋቋም ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የጤና ተቋማትን ከቀድሞው የተሻለ አድርጎ መልሶ ለመገንባት ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በጦርነቱ የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ የማቋቋም ሥራው ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት የጤና ሥርዓቱን ይጎዳዋል ነው ያለው ጤና ቢሮ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጠው መግለጫ፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ መልካሙ አብቴ (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳይ በሰጡት መግለጫ ሰላም ሲጠፋ በመጀመሪያ የሚጎዳው ጤና እና የጤናው ዘርፍ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ጤና ሲባል ሰው ነው፣ ሰላም ሲጠፋ የሚጎዳው ደግሞ ሰው ነው ብለዋል፡፡
የሰላም እጦት በሚኖር ጊዜ አምቡላንሶችን ጨምሮ ሌሎች ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ያነሱት ዶክተር መልካሙ አምቡላንሶች መንቀሳቀስ አልችል ሲሉ የሚወልዱ እናቶች በጤና ተቋማት እንዳይወልዱ ይኾናሉ፣ በጤና ተቋማት አልወልድ ሲሉ ደግሞ ለሞት ይዳረጋሉ ነው ያሉት፡፡ በጊዜ መታከም ያለባቸው ሕፃናት እንዳይታከሙ እንደሚያደርግና በሕፃናት ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር እንደሚፈጥርም ነው የተናገሩት፡፡
የደም ግፊት፣ የስኳር፣ የልብ ሕመም እና ሌሎች ሕመሞች ያሉባቸው እና በጤና ተቋማት ክትትል የሚያስፈልጋቸው ወገኖች የጤና ክትትል ማድረግ እንደማይችሉም ገልጸዋል፡፡ የሰላም እጦት ሲኖር በጤና ተቋማቱ የመድኃኒት ስርጭት ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሚኾንም ተናግረዋል፡፡ የጤና ተቋማቱ ያላቸውን መድኃኒት እየተጠቀሙ ስለኾነ እንጂ መድኃኒት ለማቅረብ ችግር መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የልብ እና የሳንባ ሕመም ያላባቸው ወገኖች ኦክስጅን እንደሚያስፈልጋቸው የተናገሩት ኃላፊው የሰላም እጦቱ ኦክስጅን ለማጓጓዝ እንደማያሰችልም ተናግረዋል፡፡ ኦክስጅን ከሚመረትባቸው ከተሞች በመነሳት ወደ ጤና ተቋማቱ ለመውሰድ አስቸጋሪ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ ደም ለማቅረብም አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል፡፡ የሰላም እጦት በሚኖር ጊዜ ደም በእጅጉ እንደሚያስፈልግም ነው ያስረዱት፡፡ ሁሉም የጤና ተቋማት ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ሲሰጡ መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በክረምት ወቅት የጤና ተጋላጭነት እንደሚሰፋ ያነሱት ዶክተር መልካሙ ወረርሽኝ የመከሰት እድሉ ሰፊ እንደኾነም አስታውቀዋል፡፡ ከክረምቱ ጋር በተያያዘ ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች የኮሌራ ወረርሽኝ ምልክቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ የወረርሽኝ ችግር እንዳይከሰት አስቀድመው ሲሠሩ መቆየታቸውን እና አሁንም እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ጤና ቢሮው የቅድመ መከላከል ሥራው ላይ በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የኮሌራ ምልክት ያለባቸው ሰዎች ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከክረምቱ ጋር ተያይዞ የወባ ወረርሽኝ በክረምቱ ከፍ እያለ መሄድንም አንስተዋል፡፡ የወባ ወረርሽኝም የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራውን በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ የወባ ወረርሽኝ መስከረምና ጥቅምት ወራት ላይ እንደሚጨምር የተናገሩት ኃላፊው የቅድመ ዝግጅት ሥራውን አስቀድሞ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ማኅበረሰቡ የአካባቢ ንጽሕናን በመጠበቅ የወባ ወረርሽኝን መከላከል እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡ የኬሚካል ርጭት ለሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ኬሚካል ለማቅረብ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የአጎበር ስርጭትም እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት እየሄዱ ክትትል እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!