
ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ለአሚኮ እንዳስታወቀው በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የኮሌራ፣ የወባና የኩፍኝ በሽታ በወረርሽኝ ደረጃ ተከስቷል፡፡ ኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስቧል፡፡
የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ለአሚኮ በሰጡት መረጃ የኮሌራ በሽታ በክልሉ በምዕራብ ጎንደር – ቋራ፤ ባሕር ዳር ዙሪያ – አንዳሳ እና በማዕከላዊ ጎንደር አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቷል ብለዋል፡፡
የተከሰተዉ በሽታ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠርና ስርጭቱን ዜሮ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
በክልሉ ኮሌራን ጨምሮ ሌሎችም የወባና የኩፍኝ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ያሳሰቡት አቶ በላይ በዛብህ በተለይም በተፈናቃይ የመጠለያ ጣቢያዎች፤ በሰፋፊ የቆላማ አካባቢ የእርሻ ቦታዎችና በትላልቅ የዞን ከተሞች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
ኢኒስቲትዩቱ በሽታ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉ ተንቀሳቃሽ የጤና ባለሙያዎች ቡድን በማሰማራት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ አበረታች ውጤት እንደታየበትም ተናግረዋል፡፡
የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ተጋላጭ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለከፍተኛ ሕመምና ሞት እንደዳረገም ነው የተናገሩት፡፡
በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት በጤናው ዘርፍ የሕይወት አድን የጤና አገልግሎት ለመስጠት እንቅፋት ስለመኾኑም ነው የተናገሩት፡፡
የሰላም እጦት በአንድ በኩል ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ማስቸገሩ በሌላ በኩል ደግሞ ለበሽታው ተጨማሪ ተጋላጮችን እየፈጠረ ስለመኾኑም ነው ያሰረዱት፡፡
ኅብረተሰቡ ከበሽታው አጋላጭ ድርጊቶች በመጠንቀቅ፤ ምልክቶችና ስጋቶች ሲታዩም በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራና ሕክምና ማድረግ እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡
ተቋሙ የተከሰቱ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም የግብዓት እጥረት እንዳያጋጥም ከዓለም አቀፍ የጤና ግብዓት ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!