ዘላቂ ሰላም ለማጽናት ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

42

ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ነዋሪዎች የተሳተፉበት ሕዝባዊ ውይይት በባሕርዳር ከተማ ተካሂዷል። የልዩነትሐሳብ ካላቸው አካላት ጋር በመወያየት እና በመመካከር ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ ነው የውይይቱ ተሳታፊዎች ያነሱት።

ውይይቱን የመሩት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል አሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እና የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር) ናቸው።
ዶክተር ሰማ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት ክልሉ ወደ ከፋ የኢኮኖሚ ድቀት እንዲገባ የሚያደርግ በመኾኑ ሁሉም በጋራ ቆሞ ለሰላሙ ሊሠራ ይገባል ብለዋል። ማንኛውም አይነት ልዩነት በውይይት እና በምክክር እንዲፈታ የክልሉ መንግሥት ጠንካራ አቋም ይዞ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የተፈጠረውን ግጭት ለማባባስ የሚጥሩ አካላት ለሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት በማሰብ ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል። ሕዝቡ የሚያነሳቸው ሁሉም አይነት ጥያቄዎች ትክክልና ፍትሐዊ መኾናቸውን በማመን የአማራ ክልል መንግሥት ከሕዝቡ ጎን ኾኖ ለመፍትሔዎች እየታገለ እንደሚገኝም ዶክተር ሰማ ተናግረዋል።

አቶ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው የአማራን ሕዝብ ትልቅነት የሚመጥኑ ውይይትና ምክክሮችን በማድረግ ከግጭትና አለመረጋጋት በዘላቂነት መላቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል። በአማራ ክልል ሁሉም አካባቢዎች ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉ የገለጹት አቶ ይርጋ አመራሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲችል የሕዝብ ድጋፍ እና አጋርነት ያስፈልገዋል ሲሉም ተናግረዋል።

“ጥሩ መሪ ለመኾን የሚደግፍ፣ የሚያጀግን እና አይዞህ የሚል ሕዝብ ይፈልጋል” ያሉት አቶ ይርጋ የራስን መሪ ስም ማጥፋት እና ማሳደድ መሪ አልባ ሕዝብ ከመፍጠር የዘለለ ረብ ያለው ክልላዊና ሀገራዊ ልማት ማምጣት እንደማይቻል አንስተዋል።

በተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በባሕርዳር ከተማ ውስጥ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትና ፋብሪካዎችም ጭምር ስለመውደማቸውም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል። ማንኛውምንም አይነት ልዩነት ወደ ጠረጴዛ በማምጣት እንዲፈታ መታገል ይገባል እንጂ ነፍጥ አንስቶ ለንጹሃን ጭምር ሞት ምክንያት መኾን የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል። የተከሰተው ግጭት እንዳይደገም የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ወጣቶችን በመምከር እና በማስከን ተገቢውን ሰላም የማስፈን ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ዶክተር ድረስ መልእክት አስተላልፈዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች ለክልሉ ሰላም እና ልማት ሁሉም በአንድነት ቆሞ መረባረብ እንዳለበት አንስተዋል። ከሰሞኑ የተከሰተው ግጭት እና አለመረጋጋት ምንጩ ምን እንደኾነ በመለየት በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባም ተጠቁሟል። ግጭቱ ዳግም እንዳይከሰት ለማድረግ መሠራት ስለሚገባቸው ጉዳዮችም የውይይቱ ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ከተነሱ ሐሳቦች መካከልም:-

👉 የግጭት እና አለመረጋጋቱ መከሰት ዋነኛ ምክንያት በመነጋገር እና መወያየት ችግሮችን የመፍታት ባሕላችን እየተዳከመ በመምጣቱ ስለኾነ የውይይት በሮች በሁሉም ወገን በኩል ሁሌም ክፍት መኾን አለባቸው፣

👉የአማራ ሕዝብ እንኳንስ ለራሱ ሰላም ለሌሎችም ኢትዮጵያዊያን ሰላም መኾን ዋጋ የሚከፍል መኾኑን መንግሥት ተረድቶ በየደረጃው ውይይቶችን በመዘርጋት የክልሉን ሕዝብ ጥያቄዎች ፈጥኖ መፍታት እና ሰላምን ማስፈን አለበት።

👉ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚጥሩ አካላት በየአቅጣጫው በግልጽ እየተስተዋሉ ቢኾንም መንግሥት ችላ ማለቱ ተገቢ አይደለም። መንግሥት ሕዝባዊ አንድነትን የሚንዱ እና በሕዝብ መካከል ቁጣን በመቀስቀስ ለግጭት የሚሠሩ ግለሰቦችን በቁርጠኝነት ማረም እንዳለበትም ተነግሯል።

👉 መንግሥት ጠንካራ የመልካም አሥተዳደር እና የፍትሕ ሥርዓትን በየደረጃው በመዘርጋት ሕዝብን በፍትሐዊነት ማገልገል እና ወንጀለኛን ደግሞ በአፋጣኝ የመጠየቅ ሥርዓት ሊበጅ ይገባል።

👉 አንዳንድ የውጭ ኅይሎች የአማራ ከፍታ እንደማይመቻቸው እና ይሄንን ግጭት ለማባባስ እንደሚሯሯጡ ጠንቅቀን በማወቅ ከእርስ በእርስ ግጭት እና ኢኮኖሚያዊ ድቀት ራሳችንን መጠበቅ አለብን።

👉የአማራ ክልል ሕዝብ ከመሪዎቹ ጋር አንድ ኾኖ በመደጋገፍ እና በመተባበር የሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎች አፋጣኝ መልስ እንዲያገኙ ሊሠራ ይገባል፤ የሚያጠፉ እና ሕዝብን የሚበድሉ መሪዎች ሲኖሩም እንዲስተካከሉ መመካከር እና ሰላማዊ ትግል ማድረግ ይገባል እንጂ መጠላላት እና መጠላለፍ ለማንም አይበጅም ነው ያሉት።

👉 የአማራ ክልል ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በፍቅር፣ በአንድነትና በሰላም፣ በእኩልነት የመኖር መብቱ ተረጋግጦ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ለመሥራት ምቹ ኹኔታ መፈጠር አለበት። ይህ ከኾነ በአማራ ክልል ብሎም በመላው ኢትዮጵያ ፍጹም ሰላም ለማስፈን ይቻላል ሲሉ አስተያየት ሰጭዎች አብራርተዋል።

👉 የጥላቻ ንግግሮችን እና አልባሌ የፍረጃ ቃላት ውርዋሮዎችን ፈጽሞ በመተው፣ በመከባበር እና በመፋቀር ላይ የተመሰረተ ውይይት እና እርቅ እንደሚያስፈልግም ተጠቅሷል። ነፍጥ ያነሳን አካል ከተጨማሪ ነፍጥ በፊት የፍቅር ጥሪ በማድረግ የማርገብ እና ጠላትን የማሳፈር ጥበብ መላበስ ያስፈልጋልም ተብሏል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጎንደር ከተማ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት በቅርሶች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም” በጎንደር ከተማ የዓለም አቀፍ ቅርሶች አስተዳደር
Next articleደብረ ብርሀን ከተማ ወደ አንፃራዊ ሰላም ተመልሳለች።