“በጎንደር ከተማ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት በቅርሶች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም” በጎንደር ከተማ የዓለም አቀፍ ቅርሶች አስተዳደር

34

ባሕር ዳር: ነሃሴ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰሞኑ በጎንደር ከተማ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት “በቅርሶች ላይ ደርሷል” የሚል የተሳሳተ መረጃ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወር ተስተውሏል።

በጎንደር ከተማ ቅርሶችና የሃይማኖት ተቋማት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተደርጎ በአንዳንድ አካላት የሚሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ እና የኮማንድ ፖስቱ ምክትል ሰብሳቢ ባዩ አቡሀይ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ የዓለም አቀፍ ቅርሶች አስተዳደር አስተዳዳሪ ጌታሁን ስዩም በሰጡት መረጃ በከተማዋ ጥንታዊ ቅርሶች ላይ ጉዳት አለመድረሱን አረጋግጠዋል።

አቶ ጌታሁን በጎንደር ከተማ ዘጠኝ ቅርሶች በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተመዝግበው የሚገኙ መሆኑን ገልፀዋል።

እነዚህም ቅርሶች ጎንደር ከተማን የቱሪዝም ማዕከል በማድረግ የላቀ አስተዋጽዖ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ከቱሪዝም እንቅስቃሴ አንፃር በከተማዋና አካባቢው የሚነሱ ማናቸውም አለመረጋጋቶች በዘርፉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ መሆኑን አብራርተዋል።

በጎንደር ከተማና አካባቢው ሰሞኑን በተፈጠረው አለመረጋጋት በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ እንከን የፈጠረ ቢሆንም በቅርሶች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ሲሉ በተለይም ለኢዜአ ገልጸዋል።

የሰላም ጉዳይ ለቱሪዝም እንቅስቃሴ እድገትና ልማት የላቀ አስተዋጽዖ እንዳለው የገለጹት አስተዳዳሪው፤ የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ዘርፉን የሚጎዳ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በጎንደር ከተማና አካባቢው ሰሞኑን የተፈጠረው አለመረጋጋት በቅርሶች ላይ ጉዳት ባያስከትልም የቱሪዝም እንቅስቃሴውን በእጅጉ አስተጓጉሏል ብለዋል።

በጎንደር ከተማ የሚገኙ ሁሉም ቅርሶች የሚጠበቁት በሕዝቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የሀገርና የዓለም ሃብት የሆኑ ቅርሶችን ሁሉም የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ባሕርዳር ከተማ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደመ ሰላሟ ተመልሳለች” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር)
Next articleዘላቂ ሰላም ለማጽናት ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።