
ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር) የባሕርዳር ከተማን ወቅታዊ የሰላም ኹኔታን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደመ ሰላሟ ተመልሳለች ሲሉ ነው የተናገሩት።
ዛሬ ነሐሴ 8/2015 ዓ.ም ባንኮች ክፍት ኾነው ደንበኞቻቸውን እያስተናገዱ ስለመኾኑም ተናግረዋል። በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች፣ ካፌዎች እና ሬስቶራንቶችም እንግዶችን እየተቀበሉ በወትሯዊ መስተንግዷቸው ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ዶክተር ድረስ ተፈጥሮ የነበረው ግጭት እና አለመረጋጋት ዳግም እንዳይከሰት ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ሕዝባዊ ውይይቶች እየተደረጉ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
የከተማዋ የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት በተሟላ መልኩ ወደ ሥራ መመለሱንም ከንቲባው ተናግረዋል።
የከተማዋ የመንግሥት እና የግል ተቋማትና መሥሪያ ቤቶች ክፍት ኾነው መደበኛ አገልግሎታቸውን እየሰጡ ስለመኾኑም ዶክተር ድረስ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!