በአካባቢያቸው አንጻራዊ ሰላም በመፈጠሩ ሰብላቸውን መንከባከብ መጀመራቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ።

25

ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር በላይነህ ኀይሌ ደቡብ ጎንደር ደራ ወረዳ ገረገራ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በቅርቡ ተከስቶ በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት የመኸር ሰብላቸውን መንከባከብ አለመቻላቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል።
በተፈጠረው የሰላም ችግር ምክንያት ሰብላቸውን ለመንከባከብ የሚያስፈልጋቸውን የሰው ኀይል ማግኘት ባለመቻላቸው ተገቢውን እንክብካቤ ለማድረግ ተቸግረው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ወቅቱ በመኸር ሰብል ላይ ዩሪያ ማዳበሪያ የሚጨመርበት ቢኾንም ችግሩ በመፈጠሩ ማዳበሪያውን አግኝቶ መጨመር አለመቻላቸውን ነው የተናገሩት። አርሶ አደሩ እንዳሉት የሰላም እጦት አርሶ አደሮች ሰብላቸውን እንዳይንከባከቡ፣ ኀብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዳይመለስ እክል ፈጥሮ ነበር ብለዋል።

ሰብል ወቅቱን የጠበቀ እንክብካቤ ካልተደረገለት የሚሠጠው ምርት በእጅጉ ይቀንሳል የሚሉት አርሶ አደር በላይነህ አርሶ አደሮች የመኸር ወቅቱ የሚፈልገውን የእርሻ እንክብካቤ እንዲያከናውኑ የሚመለከታቸው አካላት በሰላም ዙሪያ በመመካከር ክልሉን ወደ ቀደመ ሰላሙ መመለስ ይገባቸዋል ብለዋል።
ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ ነው የሚሉት አርሶ አደሩ ሰላምን ለማምጣት ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል።

በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የሮቢት ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ቻሌ አበበ እንቅስቃሴ በመገደቡ ምክንያት ሰብላቸውን ለመንከባከብ የሚያስፈልገውን የሰው ኀይል ለማግኘት ተቸግረው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ወቅቱ ዩሪያ ማዳበሪያ የሚጨመርበት ቢኾንም በሰላም እጦት ምክንያት ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል። የሰላም ዋጋው ብዙ ነው የሚሉት አርሶ አደሩ ሠርቶ ለመብላት እና በሰላም ወጥቶ ለመግባት፣ ነገን የተሻለ ለማድረግ ሰላም አስፈላጊ ነው ይላሉ።

ዛሬ በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውም እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል። አሁን የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠልም ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል ድርሻ ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየምክር ቤቱ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።
Next article“ባሕርዳር ከተማ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደመ ሰላሟ ተመልሳለች” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር)