ምርትን በሚፈለገው መንገድ ለማንቀሳቀስ ሰላም ወሳኝ መኾኑን የምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ባለሀብቶች ተናገሩ፡፡

38

ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ባለሀብቶች ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት ከሰሞኑ ተከሰቶ በነበረው የሰላም መደፍረስ በሚፈልጉት ሁኔታ ምርት ወደ ገበያ ለማቅረብ አስቸግሯቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ባለሀብቶቹ እንዳሉት ሰላም ሲኖር ለሥራ የሚፈልጉትን የሰው ኃይል ማግኘት ያስችላቸዋል፡፡

ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ምርቶችንም ማንቀሳቀስ የሚቻለው ሰላም በአካባቢው ሲኖር እንደኾነም አስረድተዋል፡፡

የሰላም ባለቤቱ ራሱ ሕዝቡ መኾኑን የተናገሩት ባለሀብቶቹ ሰላምን ለማረጋገጥ ሰክኖ በችግሮች ዙሪያ ተወያይቶ መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ሕዝቡ ሰላሙን ለማረጋገጥ መረጃ ከመንግሥት አካል ጋር መለዋወጥ እንደሚገባው የገለጹት ባለሀብቶቹ ለሰላሙ ጠንቅ የኾኑ አካሄዶችን መከታተልና ማረም፤ ለሕግ የሚቀርቡትንም ለሕግ ማቅረብ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

በሽምግልና የሚመለሱትን እየመከሩ ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም አስገንዝበዋል፡፡ በምክክር የሚመለሰውን እየመከሩ መመለስ እንደሚገባም ነው የነገሩን፡፡

የሰላም እጦት ሲኖር ምርትን ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ ለማዘዋወር አስቸጋሪ ስለሚሆን ሕዝቡን ላልተፈለገ የዋጋ ጭማሪ ይዳርጋል ያሉት ባለሃብቶቹ አሁን ላይ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም የዋጋ ጭማሪውን ለመቆጣጠር አይነተኛ መፍትሄ ስለመኾኑም አስረድተዋል፡፡
ኅብረተሰቡ የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleውይይትን የችግሮች መፍቻ ቁልፍ ማድረግ እንደሚገባ የመርዓዊ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
Next articleየምክር ቤቱ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።