
ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ የሰላም መደፍረስ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መካከል መርዓዊ እና አካባቢው አንዱ ነው፡፡
በአካባቢው በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ከሳምንት በላይ እንቅስቃሴ ተገትቶ መቆየቱን ነው ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች የገለጹት፡፡
በአንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል፡፡
በሕጻናት እና በአቅመ ደካሞች ላይም የሥነ ልቦና ጫና ደርሷል፡፡
ይሁን እንጅ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የጸጥታ አካላት በጋራ በሠሩት ሥራ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ የንግድ ተቋማት ወደ ሥራ ተመልሰዋል ብለዋል፡፡
ተሽከርካሪዎችም አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ነግረውናል፡፡
ነዋሪዎቹ የሚፈጠሩ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንጅ በኃይል የሚደረግ እንቅስቃሴ ውጤቱ ኪሳራ መኾኑን ካለፉት ተሞክሮዎች መማር ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ወጣቶች የሚፈጠሩ ችግሮችን በውይይት መፍታት ባሕል ማድረግ እና ሰላምን አማራጭ የሌለው ብቸኛ መንገድ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!