
ባሕር ዳር: ነሐሴ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተወሰኑ ከተሞች ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የከተሞችን አሁናዊ ሁኜታ አሚኮ እየተከታተለ መረጃዎችን እያደረሰ ይገኛል። የባሕርዳር ከተማን የሰላም ሁኔታ በተመለከተም አሚኮ ነሐሴ 6/2015 ዓ.ም ከከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳሕሉ ጋር ቆይታ አድርጎ የተዘጉ መንገዶች እየተከፈቱ እንደሚገኙና አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ወደ ሥራ እንደሚመለሱ ተገልጾ ነበር። ዛሬ ነሐሴ 7/2015 ዓ.ም ደግሞ አሚኮ የከተማዋን እለታዊ ኹኔታ ተመልክቷል።
በምልከታውም በከተማው ተዘግተው የነበሩ መንገዶች ሙሉ በሙሉ ተከፍተዋል። ይህንን ተከትሎም የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጀምሯል።
ዛሬ እሁድ እንደመኾኑም በከተማው ውስጥ የሚገኘው ሰንደይ ማርኬት ተከፍቶ በግብይት ላይ ነው።
ቀበሌ 04 አካባቢ የሚገኙ ትልልቅ ሱቆች አንዳንዶቹ ክፍት ሆነው ሰላማዊ ግብይት ላይ ሲኾኑ አንዳንዶቹ ግን እንደተዘጉ ናቸው።
ሆቴልና ካፌዎችም ክፍት ሆነው ደንበኞቻቸውን እያስተናገዱ ይገኛሉ።
በባሕርዳር ከተማ በዘንባባዎች እና በሌሎች ዛፎችም ጥላ ሥር በጀበና ቡና እንግዶቻቸውን የሚያሳርፉ ታታሪ ሴቶች አብዛኞቹም ዛሬ በሥራ ላይ ናቸው። በከተማው ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታክሲዎች ተጓዦችን ሰልፍ እያስያዙ የተለመደውን ሥራቸውን በፍፁም ሰላማዊ ሁኔታ እየሠሩ ነው። ይሁን እንጅ የታክሲዎች ቁጥር የወትሮውን ያህል ባለመኾኑ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች በእግር ጉዞ እየተንቀሳቀሱ ነው። እቃዎችን ከቦታ ቦታ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎችም በከተማው ውስጥ እየተንቀሳቀሱ እየሠሩ ነው።
በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰን እንደታዘብነው ለወትሮው ሰለማዊ በነበረችው ባሕርዳር ከተማ ውስጥ የተፈጠረው ድንገተኛ አለመረጋጋት ነዋሪዎቿን ለሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት ጉዳት አጋልጦ ነበር። አሁን ላይም ከተማዋ ወደ ቀደመ ሰላሟ ተመልሳለች።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!