ጎንደር ከተማ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ መመለሷን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

88

ባሕር ዳር: ነሃሴ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ቀናት ጎንደር ከተማ ላይ አለመረጋጋት በመፈጠሩ ሰዎች ቤት ዘግተው እንዲቀመጡ ማድረጉን ነዋሪዎቹ ነግረውናል፡፡ ነዋሪዎቹ በነበረው ችግር ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት መከሰቱንም መታዘባቸውን አስረድተዋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው በተከሰተው ጦርነት ከስነልቦና አንጻርም ከፍተኛ ጉዳት መፍጠሩንም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ነዋሪዎቹ በትዝብታቸው እንዳሉት ሁኔታው ድንገተኛ ስለነበር የዕለት ምግብ እንኳን ለማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር ነው የገለጹት፡፡

የከተማው ነዋሪ ሴቶች፣ አቅመ ደካሞች እና ሕፃናት በሁኔታው የበለጠ ተጎጅ እንደነበሩ ነው ለአሚኮ ትዝብታቸውን የተናገሩት፡፡ በተለይ ሕይዎት መጥፋቱን እና በከተማው ባሉ ሕንጻዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ማየታቸውን ነው ያብራሩት፡፡ አሁን ላይ ጎንደር ከተማ ከነበረባት ያለመረጋጋት ችግር ወጥታ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መጀመሯንም አስረድተዋል፡፡

እንደነዋሪዎቹ ገለጻ፡-
✍️በከተማዋ ያሉ የፍጆታ እቃ የሚሸጡ ሱቆች ተከፍተዋል፡፡
✍️አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎች ተከፍተዋል፡፡
✍️ሰው በነጻነት ተንቀሳቅሶ የሚፈልገውን እቃ ሲገዛ ይስተዋላል፡፡
✍️ወደ እምነት ተቋማት የሚያቀኑ ሰዎችም ያለስጋት ወደየ ቤተ እምነታቸው ሲጓዙ ይስተዋላል፡፡
✍️አገልግሎት ሰጭ ታክሲዎችም ወደ ሥራ እየተመለሱ ስለመኾናቸው አስረድተዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ሰላሙ እንዲመጣ ነዋሪው ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ገልጸው ወደፊትም እንዲህ አይነት ችግር እንዳይከሰት ሁሉም አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ እንደሚገባው ነው ያስገነዘቡት፡፡ ሰላም ለሁሉም ነገር ወሳኝ መኾኑን ባለፉት ቀናት አይተናል ያሉን ነዋሪዎቹ አሁንም መንግሥት እና ማኅበረሰቡ ተናበው እየተመካከሩ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አስረድተዋል፡፡ ልዩነት ያለው ማንኛውም አካል ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ከማቅረብ ውጭ በመሳሪያ ማድረግ ከምንም በላይ የከተማዋን ነዋሪ የሚጎዳ በመኾኑ ለከተማው ሕዝብ ሊያስቡ እንደሚገባም ነው ሀሳባቸውን የሰጡን፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለሰላም ለሚሰጠው ትልቅ ዋጋ የደሴን ሕዝብ እናመሰግናለን” ሳሙኤል ሞላልኝ የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ
Next articleገንዳውኃ ከተማ ወደሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰች መኾኑን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡