“ለሰላም ለሚሰጠው ትልቅ ዋጋ የደሴን ሕዝብ እናመሰግናለን” ሳሙኤል ሞላልኝ የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ

74

ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከሰሞኑ በተፈጠረው የሰላም እጦት አንዳንድ ከተሞች ሰላማዊ እንቅስቃሴያቸው ተገትቶ ቆይቷል፡፡ ከቀናት በኋላ በተፈጠረው መረጋጋት የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው የነበሩ ከተሞች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴያቸው ተመልሰዋል፡፡ የታሪክ፣ የፍቅር፣ የደግነት፣ የአንድነት እና የውበት መገኛዋ ደሴ ከተማ ሰላሟን ጠብቃ ሰንብታለች፡፡ ዛሬም እንደ ቀደመው ሁሉ ነዋሪዎቿ በፍቅርና በደግነት ሰላማዊ እና መደበኛ ሕይወታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ደሴ መገለጫዋ የሆነውን ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት ዛሬም እንደጠበቀችው ናት፡፡ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ደሴ ከተማ ሰላሟን ጠብቃ መደበኛ እንቅስቃሴ ሲካሄድባት እንደቆየች እና አሁንም ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች በአጠቃላይ የከተማዋ ሕዝብ መደበኛ ሥራውን እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በከተማዋ ዛሬም ሆነ ባለፉት ቀናት የተፈጠረ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር አለመኖሩንም አስታውቀዋል፡፡ ለሰላም ለሚሰጠው ትልቅ ዋጋ የደሴን ሕዝብ እናመሰግናለንም ብለዋል፡፡
የከተማዋ ሕዝብ የከተማዋን ሰላም በመጠበቅ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የፀጥታ መዋቅሩም የወትሮ ሥራውን እየሠራ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በጋራ መቆም እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡ የአማራን ሕዝብ ወደ ግጭት ውስጥ መክተት አግባብ እንዳልሆነና ሰላም ወዳድ የሆነውን ሕዝብ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማስፈታት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ የደሴ ከተማ ሕዝብ ለሰላም በትኩረት እንደሚሰራም፤ ለውይይት ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡ ጥያቄዎችን ለማስመለስ ሰከን ብሎ መወያየት እና ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ግጭት እና የሰላም እጦት ለአማራ ሕዝብ ክብር እንደማይመጥንም ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የደብረማርቆስ ከተማ ወደቀደመ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ ተመልሳለች” ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ
Next articleጎንደር ከተማ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ መመለሷን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡