“የደብረማርቆስ ከተማ ወደቀደመ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ ተመልሳለች” ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ

119

ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረማርቆስ ከተማ ባለፉት ቀናት የሰላም እጦትና አለመረጋጋት እንደነበረ የተናገሩት የደብረማርቆስ ከተማ ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ ከሁለት ቀናት ወዲህ ግን ከተማዋ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለስ መጀመሯን አስረድተዋል፡፡
ከንቲባው እንዳሉት፡-

👉 ሕዝቡ በሰላማዊ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
👉 ሱቆች ተከፍተዋል።
👉 ባንኮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ሥራቸው ተመልሰዋል፡፡

በተለይም ከሀገር ሽማግሌዎች ከወጣቶች፣ ከሚመለከታቸው የከተማው ነዋሪዎች ጋር እና ከተለያየ የአደረጃጀት አባላት እና አመራሮች ጋር እየተገናኙ በከተማው ሰላም ላይ እየመከሩ ስለመኾኑም ከንቲባው ለአሚኮ አብራርተዋል፡፡
👉 አሁን ባለው ሁኔታ ሕዝቡ የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ ባደረገው ርብርብ ከተማዋ ወደ ቀደመ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ መመለሷንም አስረድተዋል፡፡

ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ እንደነገሩን ባለፉት ቀናት በከተማዋ በነበረው አለመረጋጋት ከፍተኛ ውድመት እንደተከሰተ ነው የገለጹት፡፡ የመንግሥት ተቋማት እና የመንግሥት ተሽከርካሪዎች ሰፊ ውድመት እንደደረሰባቸውም ነግረውናል፡፡
👉 በተለይም አብማ በተባለ ክፍለ ከተማ እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው ንብረት ሙሉ ለሙሉ መውደሙን ነግረውናል፡፡
👉 ቀበሌ 2 እና 6 ያሉ የመንግሥት ተቋማትም የተወሰነ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
👉 የምሥራቅ ጎጃም አሥተዳደርም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወድሟል፡፡
👉 ብዙ ቅርስ የነበረበት የንጉስ ተክለሃይማኖት ቤተመንግሥት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ እንዲወድም ተድርጓል፡፡
👉 የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ከመዘረፍ አልፎ ወድሟል፡፡

ከንቲባው የጠፋውን ንብረት የከተማው ሕዝብ እንዲያይ እና እንዲህ አይነት ሁኔታ መደገም እንደሌለበት ትምህርት እንዲወሰድበት እየተደረገ እንደኾነም ነው ያብራሩት፡፡ ወደፊትም እንዲህ አይነት ነገር እንዳይደገም ትምህርት እንዲወሰድበት የከተማው ማኅበረሰብ እንዲያየው ጥረት እየተደረገ እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡ ባለፉት ሦስት ቀናት የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠልም ከሕዝቡ ጋር ለመወያየት እና ለመምከር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ማስመለስ የሚቻለው በዚህ መንገድ አይደለም ያሉት ከንቲባው አንድ ኾኖ የጋራ ችግርን በጋራ መፍታት ሲቻል መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ አንድ ሆኖ ሰላሙን እንዲያረጋግጥ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ከሕዝብ ጋር ለመምከር እየተንቀሳቀሱ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የባሕርዳር ወዳጆች ሁሉ ለባሕርዳር ከተማ ፍፁም ሰላም መኾን እየሠሩ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር)
Next article“ለሰላም ለሚሰጠው ትልቅ ዋጋ የደሴን ሕዝብ እናመሰግናለን” ሳሙኤል ሞላልኝ የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ