
ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ሰላም በመመለሱ ሁሉም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ እንቅስቃሴ እየተደረገ መኾኑን ከተማ አሥተዳደሩ ገልጿል። የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር) ከተማዋ ወደ ቀደመው ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ መመለሷን ተናግረዋል። የተፈጠረው ግጭት እና አለመረጋጋት በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ያስከተለ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ለከተማዋ የፀጥታ ስጋት ሊሆን የሚችል ነገር እንደሌለ ነው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የተናገሩት። ዶክተር ድረስ ከተማዋ ወደተሟላ ሰላሟ ተመልሳ ልክ እንደወትሮው ነዋሪዎቿ በሰላም ተረጋግተው የሚኖሩባት፤ ጎብኝዎቿም በፍቅር የሚስተናገዱባት ከተማ እንድትኾን በየክፍለ ከተማ እና ቀበሌዎች ውይይቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
“የባሕርዳር ወዳጆች ሁሉ ለባሕርዳር ከተማ ሰላም መኾን እየሠሩ ነው” ያሉት ዶክተር ድረስ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ከከተማው አመራሮች ገር ውይይቶችን በመጀመር የንግድ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሥራ እንዲጀምሩ እየተደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል። አሁን ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩን እና ሱቆችም መከፈታቸውን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።
ለባሕርዳር ከተማ ሰላም መኾን የሚጥሩት በርካታዎች ቢሆኑም ወቅታዊ ሁኔታውን በመጠቀም መሰረታዊ ምርቶችን የሚደብቁ እና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ የሚፈጥሩ አካላት ስለመኖራቸውም ከንቲባው ጠቁመዋል። እንዲህ አይነትቱን ጊዜ በመደጋገፍ እና በአንድነት ማለፍ ሲገባ በስግብግብነት ህዝብን ጎድቶ አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት የሚጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ማኅበረሰቡም በእንዲህ አይነት ድርጊት ውስጥ የተሰማሩ አካላትን በሚመለከት ጊዜ ለተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ጭምር ጥቆማዎችን በማድረስ በጋራ መከላከል የስፈልጋል ነው ያሉት። በከተማዋ ተከስቶ የነበረው ግጭት እና አለመረጋጋት ተገቢ እንዳልነበር የገለጹት ከንቲባው በቀጣይም እንዲህ አይነት የሃሳብ ልዩነቶች ሲኖሩ ውይይቶችን ማስቀደም ነው የሚበጀን ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!