
ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች አሳሳቢ እየሆኑ መጥተዋል ብለዋል።
ብዙ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች ይኖራሉ፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ግን ጠቃሚው መንገድ ሰላማዊ ውይይት ነው ብለዋል፡፡
አቶ ደመቀ ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ የጥያቄዎችን መፍቻ መንገድ የሚያደናቅፍ፤ ያለንን የሚያሳጣ፤ በዘላቂነት ሊታዩ ይገባቸዋል የምንላቸውን ጉዳዮች እንዳይፈቱ የሚያወሳስብ አካሄድ ነው ብለዋል፡፡
‘ሰላም ከሌለህ ሁሉን ታጣለህ’ የሚባለውን እውነታ ከልብ በማጤን በአስተውሎት መጓዝ በሚገባን ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን ነው ያሉት፡፡
በየዘመኑ ብዙ ፈተናዎች እና ችግሮች ሲገጥሙ በጥበብ ተሻግረው ያሻገሩንን የአባቶቻችን ጥበብና አስተውሎት ማጥበቅ ይጠይቃል ያሉት አቶ ደመቀ የሀገር ሽማግሌ የጠፋበት፣ ታላቅ የሌለበት፣ መካሪ የሃይማኖት አባት የታጣበት ይመስል ሁላችንንም የሚያባላና የሚበላ አካሄድ ይስተዋላል ብለዋል፡፡
የዚህ መጨረሻ በግራም በቀኝም ከውጭም ከውስጥም ላሰፈሰፉ ኃይሎች ሰርግና ምላሽ ሆኖ አቅም የሚያሳጣ፣ ክብራችንን የሚጎዳ፣ ተጋላጭነታችንን የሚያሰፋ በአጠቃላይ ሁሉንም የሚያሳጣ እንዳይሆን ያሰጋል ነው ያሉት፡፡
ከለውጡ ብዙ የጠበቅናቸው ግን ደግሞ ምላሽ ያላገኘንባቸው ያላረኩንና ሌሎች ችግሮችና ስሜቶች ይኖራሉ፤ ለእነዚህ ጉዳዮች ቆም ብለን በማሰብ በሰላሙ መንገድ ዘላቂ መፍተሄ እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም የሁሉም ዋስትና የሆነውን ሕግና ሥርዓት በተሟላ መልኩ ማክበርና ማስከበር ይገባል ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!