
ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ2016 በጀት ዓመት ከኢንዱስትሪ ወጪ ምርቶች ከ450 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት መታቀዱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
ሚኒስቴሩ የ2015 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምና የ2016 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ ከክልልና ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮዎችና ተጠሪ ተቋማት ጋር በሚዛን አማን ከተማ ተወያይቷል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የማምረት አቅምን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አምጥተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገበውን 55 በመቶ የማምረት አቅም በ2016 በጀት ዓመት ወደ 58 በመቶ ከፍ ለማድረግ ግብ መቀመጡን አስታውቀዋል።
የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን መፍታት በአዲሱ በጀት ዓመት ትኩረት እንደሚሰጠውም አቶ መላኩ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ለኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክና የመንገድ መሠረተ ልማት በማሟላት ፍላጎትን ያማከለ የማምረት አቅም ለመፍጠር ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ450 ሚሊዮን ዶላር በላይ የወጪ (ኤክስፖርት) ምርቶችን አምርቶ ወደ ውጭ ለመላክ መታቀዱንም አስታውቀዋል።
ከዘርፉ በ2015 በጀት ዓመት የተገኘው 335 ሚሊዮን ዶላር እንደነበርም ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።
በበጀት ዓመቱ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ሥራ ይከናወናልም ብለዋል።
ለእዚህም የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በሁሉም ክልሎች በልዩ ትኩረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስታወቁት።
የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ የእቅድና በጀት ዳይሬክተር አቶ አብዱልሃሊም ሀሰን በ2015 የታዩ “የኢትዮጵያ ታምርት” ውጤቶችን ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ለኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ተግባር ትኩረት እንደሚደረግበትም ነው የገለጹት።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛው ጋኪያብ በበኩላቸው “በክልሉ ያለውን ፀጋ መሠረት ያደረገ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ከባለድርሻ አካላት ጋር ይሰራል” ብለዋል።
በክልሉ ለሚሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግና ግብዓት በማሟላት ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማገዝ ቢሮው ዝግጁ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ ላለፉት ሁለት ቀናት ያካሄደው የዕቅድ ግምገማ መድረክ የ2016 በጀት ዓመት መሪ እቅዶች ላይ በመምከር ተጠናቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!