
ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም ባለፉት ጊዜያት ጀምሮ በክልሉ የፀጥታ ችግር አጋጥሟል ብለዋል። መንገድ በመዝጋት የሰዎችን እንቅስቃሴ በመግታት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳት አድርሷል ነው ያሉት። ያለው ግጭት እርስ በእርስ እያገዳደለና ሰብዓዊ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑን ገልፀዋል።
እርስ በእርስ መጠፋፋት ዘላቂ ችግር እንጂ ዘላቂ ሰላም አያመጣም ነው ያሉት። ሁሉም ለሰላም መረባረብ አለብንም ብለዋል። የክልሉ የፀጥታ መዋቅርና የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም አስታውቀዋል። የክልሉ ሕዝብ እየተደረገ ያለውን ሕግ የማስከበር ሂደት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረግ መሆኑን ማወቅ ይገባል ነው ያሉት።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን የተውጣጣ የኢትዮጵያውያን ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ መከላከያን ያለ ስሙ ስም መስጠትና መተንኮስ አግባብ አይለምም ብለዋል። የፀጥታ ችግርን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባም ገልፀዋል።
የክልሉ መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል። ሁሉም ጥያቄ አለኝ የሚል ችግሮቹን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መረባረብ አለበት ነው ያሉት።
ልዩነት ያለው አካል ሁሉ ነፍጡን አስቀምጦ ወደ ውይይት እንዲመጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ለሰላም ዘብ በመቆም ችግሮቻችን መፍታት ይገባናል ነው ያሉት። ክልሉን ዋጋ የሚያስከፍል ችግር ከመከሰቱ አስቀድሞ ሁሉም ለሰላም መረባረብ እንደሚገባው አሳስበዋል።
አሁን ያለው አካሄድ ክልሉን አደጋ ውስጥ የሚከት በመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ለሰላም እንዲሠራም ጠይቀዋል። እርስ በእርስ በመገዳደል ያመጣነው ለውጥ የለምም ብለዋል።
የክልሉ ሕዝብ ለሰላም በየአካባቢው ያለውን ትንኮሳ በማስቆም ሁሉም ወደ ሰላም እንዲመጣም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!