ጊዚያዊ ችግሮች ከዘላቂ ጥቅሞቻችን አንጻር መቃኘት እንዳለባቸው ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) አሳሰቡ።

110

ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከሁሉም ዞኖች የተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበትና በወቅታዊ ክልላዊ የሰላም ሁኔታዎች ላይ በባሕር ዳር ከተማ የተካሄደው የውይይት መድረክ ተጠናቅቋል። ውስጣዊ ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባል ያሉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በክልሉ እየታየ ያለውን ስርዓት አልበኝነት መመለስ የምንችለው ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ወደ ክልሉ የገባው የሰላም መደፍረስ ችግር ስለገጠመ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳደሩ ምንጊዜም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ማድረግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። ችግሮችን በውይይት እና በንግግር ለመፋታት የክልሉ መንግስት በሩ ክፍት ነውም ብለዋል። ውስጣዊ አንድነታችን ላይ ክፍተት በመፈጠሩ ለክልሉ ሰላም መደፍረስ ምክንያት መኾኑን ያመላከቱት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጌታቸው ጀምበር (ዶ.ር) ሰላምን ሊያደፈርሱ ከሚችሉ ድርጊቶች መቆጠብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ፋኖን የክልሉ መንግሥት ዕውቅና መስጠት ብቻ ሳይሆን የያዘው መሳሪያ ህጋዊ እንዲሆን ክልሉ አድርጓል ያሉት ዶክተረ ጌታቸው በፋኖ ስም ጥፋት የሚያደርሱ ላይ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል። እነዚህን አካላት መምከርና መገሰጽ ከሃይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ይጠበቃልም ብለዋል ምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው መሪን በመግደል እና በመሳደብ ጥያቄን መፍታት ስለማይቻል አንድነታችንን ሊሸረሽሩ የሚችሉ አካላትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል። ሰላም ማስከበር ለአንድ አካል ብቻ የተሰጠ ተግባር አይደለም ያሉት አቶ ይርጋ ፤ ሁሉም ሊጠብቀውና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ማህበራዊ አጀንዳ መሆኑን አመላክተዋል። አቶ ይርጋ አያይዘውም መከላከያ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ውቅር መሆኑን ጠቅሰው የአማራ ክልል ሕዝብ ታሪክ እና ማንነት ተጠብቆ እንዲቆይ ከሕዝባችን ጋር ሆኖ መስዋዕት የከፈለው የመከላከያ ሠራዊት ነው ብለዋል።

የወሰንና የማንነት ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፈታት አለበት በሚል ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም አቶ ይርጋ መግለጻቸውን የፓርቲው መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአንድነት በመቆም እና በትብብር በመሥራት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ።
Next article“ልዩነት ያለው አካል ሁሉ ነፍጡን አስቀምጦ ወደ ውይይት ይምጣ” ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)