
ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወቅታዊ የሰላምና ፀጥታ ኹኔታዎች ላይ የሚመክር የውይይት መድረክ በባሕርዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ከሁሉም ዞኖች የተወከሉ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል መላዕከ ሕይወት ሀብተማርያም አላምረው እንደ ክልል እና እንደሀገር ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መንግሥት እና ሕዝብ በመቀራረብ እና በመመካከር መሥራት አለባቸው ብለዋል።
በጦርነት የሚፈታ ችግር የለም ያሉት መልዕከ ሕይወት ሀብተማርያም አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ብቸኛው መንገድ መወያየትና መመካከር ነው ብለዋል። በተለይም ወጣቶች ከስሜታዊነት በመውጣት እና ሕግን በማክበር አሉኝ የሚሏቸውን ጥያቄዎች በስክነት ማቅረብ አለባቸው ነው ያሉት። መንግሥትም ወጣቶች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በማዳመጥ ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንደሚገባው አስገንዝበዋል። ሌላው ተሳታፊ ቄስ ዘላለም ፈንቴ አሁን ላይ ያለው የመንግሥት መዋቅር አልፎ አልፎ የሚከሰቱትን የሰላም መደፍረስ ምልክቶች ፈጥኖ በማረም በኩል ውስንነቶች የሚስተዋሉበት ነው ብለዋል። የሕዝብን ሰላም የሚያናጉ ምልክቶች ሲኖሩ በመንግሥት በኩል አፋጣኝ እና ፍትሐዊ እርምት መወሰድ አለበት ብለዋል።
ቄስ ዘላለም “ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ስለዚህም ሁሉም የድርሻውን በመውሰድ እና ለሰላሙ ዘብ በመቆም እንደ ክልል እና እንደ ሀገር አስተማማኝ ሰላም መትከል ያስፈልጋል ብለዋል። በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች በማዳመጥ ምላሽ ከሰጠ እና ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ጥረት ካደረገ ሰላማዊ አካባቢ እና ሀገርን መገንባት ይቻላል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የመጡት አቶ አምሳሉ ቻሌ በበኩላቸው ሲንከባለል የቆየው የማንነት ጥያቄ የሰላም መደፍረስ ዋነኛ ምክንያት ነው ብለዋል። ይህን ጥያቄ ይዋል ይደር ሳይባል በአስቸኳይ መፍታት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ አምሳሉ ወጣቶች ከማንኛውም አይነት አፍራሽ ድርጊት በመቆጠብ ሰላምን ለማፅናት ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ ፍትሐዊ ምላሽን መጠበቅ አለባቸው ብለዋል። አንድነት እና መቻቻል ለሁሉም አይነት ችግሮች መፍትሔ ለማፈላለግ ወሳኝ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል። “በሕዝቡ ዘንድ ያለው የአንድነት መንፈስ እስካሁንም እንደተጠበቀ አለ” ያሉት አቶ አምሳሉ ይህንን አንድነት ለመናድ የሚጥሩ የፖለቲካ ነጋዴዎችን በጋራ በመቆም መከላከል ያስፈልጋል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
“የሕዝብን ሰላም በማደፍረስ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ማስመለስ አይቻልም” ያሉት ደግሞ ሼህ ጀማል አልይ ናቸው። ወጣቶች መሰረታዊ ጥያቄዎች ሲኖራቸው በስክነት እና በአንድነት ማስረዳት ያስፈልጋል፤ ከዚህ ያለፈ አካሄድ ግን ጉዳዩን ወደ ሁከት እና ብጥብጥ የሚመራ ይኾናል ነው ያሉት። መንግሥት ግልፅ የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት እና ከሁሉም አካላት ጋር በመመካከር ሰላምን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ነገሮችን ቀድሞ መዝጋት እንዳለበትም ሼህ ጀማል መልዕክት አስተላልፈዋል።
አጋቢ;- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!