
ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ካዳስተር የመሬት ይዞታን መሰረት ያደረገ የመሬት መረጃ አያያዝ ሥርዓት ነው። የሚደራጁት መረጃዎችም በዋናነት የካርታ እና ገላጭ መረጃዎችን ያካተተ ነው። የካርታ መረጃ የይዞታውን መገኛ ቦታ፣ ወሰኑን፣ ስፋቱንና ቅርፁን፣ አጎራባች ይዞታዎችን እና አዋሳኝ መንገዶችን የሚያሳይ ሲሆን ገላጭ መረጃ በመባል የሚታወቀው ደግሞ የባለይዞታውን ማንነት (ስም፣ አድራሻ፣ ጾታ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ ወዘተ.)፣ በይዞታው ላይ ያለው መብት፣ ክልከላና ኃላፊነት፣ የቦታው አገልግሎትና ደረጃ እና የመሳሰሉት እንደ ካዳስተር ዓይነቱ ተዘርዝረው የሚያዙ መረጃዎችን ያካትታል፡፡ እነዚህ የመረጃ ዓይነቶችም በልዩ የይዞታ መለያ ኮድ እንዲገናኙ ይደረጋል፡፡
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ በክልል ያለውን የመሬት ይዞታ መረጃ አያያዝ ሥርዓት ለማዘመን የካዳስተር ሥራ ከጀመረ ሰባት ዓመታትን ማስቆጠሩን በቢሮው የሕዝብ ግነኙነት ኀላፊ አወቀ ሲሳይ ተናግረዋል። ኀላፊው እንዳሉት በክልሉ ከሚገኘው 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የመሬት ባለይዞታ አርሶ አደሮች ውስጥ እስከ አሁን 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ አረንጓዴ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
በክልሉ ካለው ከ18 ሚሊዮን በላይ የተበጣጠሰ ማሣ ውስጥ ደግሞ 70 በመቶ የሚኾነው ማሳ የሁለተኛ ደረጃ ይዞታ ማረጋገጫ ተሠርቶለታል፡፡ ከ148 ወረዳዎች ውስጥ በ113 ወረዳዎች የካዳስተር ሥራ መሠራቱንም ነው ኀላፊው የገለጹት። እንደ ኀላፊው ገለጻ የካዳስተር ሥራ መሠራቱ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ አቅም ፈጥሯል። አርሶ አደሮችም መሬታቸውን ዋስትና በማስያዝ የብድር ተጠቃሚ እንዲኾኑ ተደርጓል። እስከ አሁንም ከ14 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ ደብተር ዋስትና በማስያዝ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር ተጠቃሚ መኾናቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡ በቀጣይም የአርሶ አደሩን የብድር ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቅርቡ ቢሮው ከአበዳሪ ማይክሮ ፋይናንስና ባንኮች ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህም አርሶ አደሩ ትራክተር፣ የውሃ ፓምፕ እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶችንና የቴክኖሎጅ ውጤቶችን በፈለገው ጊዜ በመግዛት እንዲጠቀም ትልቅ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
አቶ አወቀ እንደገለጹት የካዳስተር ሥራ መሠራቱ በአንድ የእርሻ መሬት በተለያዩ አርሶ አደሮች ይወጣ የነበረውን አረንጓዴ ደብተር አስቀርቷል፡፡ በመሬት ጉዳይ ይጨናነቁ የነበሩ የፍርድ ቤቶች ክርክር እና በመሬት ምክንያት ይከሰት የነበረውን ግጭት ቀንሷል፡፡ የእርሻ፣ የአትክልት፣ የወል፣ የደን መሬቶችን የአጠቃቀም ሕግም ተግባራዊ በማድረግ እንዲለሙ እየተሠራ ይገኛል ፤ መንግሥት ከመሬት ማግኘት የሚገባውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትም ያሳድጋል ነው ያሉት ኅላፊው። በክልሉ የሁለተኛ ደረጃ አረንጓዴ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር አሰጣጥ ሥራ በቀጣይ አምስት ዓመታት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኘው ከ50 ሚሊዮን በላይ ቁርጥራጭ መሬቶች ውስጥ ለ28 ሚሊዮኑ የመሬት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንደተሰጠ መረጃዎች ያሳያሉ።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!