”ግዴታየን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለሁ” በሚል መሪ ሐሳብ በምዕራብ ጎንደር ዞን የገቢዎች መምሪያ የግብር ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።

404

”ግዴታየን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለሁ” በሚል መሪ ሐሳብ በምዕራብ ጎንደር ዞን የገቢዎች መምሪያ የግብር ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 19/2012ዓ.ም (አብመድ) ግብር ለኢትዮጵያ ዕድገት እና ብልፅግና የሚያበረክተው ሚና ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ቢሆንም አሁን ባለዉ ሁኔታ የሚሰበሰበዉ ግብር አነስተኛ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ ስመኘዉ አያናው በመድረኩ ገልጸዋል።

ይህ ሊሆን የቻለዉ ደግሞ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በቁርጠኝነት ተግባርና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው እንደሆነ አመላክተዋል።

ይህን ለማሻሻል መሥራት እንደሚገባና እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችንም በግብር የንቅናቄ መድረክ መደገፍ አስፈላጊ በመሆኑ መድረኩ መፈጠሩን የመምሪያ ኃላፊው ገልጸዋል።

በየጊዜዉ የሚወጡ ደንቦችንና መመሪያዎችን በመተግበር የግብር አከፋፈል ሥርዓትንና ልምድን ማሻሻል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ተወካይ አስተዳዳሪ ሆናለም አሻግሬ ደግሞ ‹‹በሀገራችን እየተመዘገበ ያለውን ልማት የበለጠ ለማጠናከርና የድርሻችን ለማበርከት በግብር አሰባሰብ ሂደቱ የእያንዳንዳችን ተሳትፎ ወሳኝነት አለው›› ብለዋል።
በግብር አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ችግሮችን መለየት እና ማረም የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅም አመላክተዋል።

በተለይም ኋላ ቀር የግብር አሰባሰብ ልምድን በማሻሻል እና ካለፈዉ ትምህርት በመውሰድ ሥርዓቱን ማዘመን መቻል እንደሚገባም አሳስበዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት በዞኑ የነበረዉ የፀጥታ ችግር በግብር አሰባሰብ ሂደቱ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ ማለፉን ያስታወሱት አቶ ሆናለም ‹‹ዞናችን አሁን ወደ ሠላም በመመለሱ የግብር አሰባሰብ ተግባራችንን በአግባቡና በተገቢው መንገድ በመፈጸም ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን›› ብለዋል።
በመድረኩ ተሳታፊዎች ሐሳብና አስተያየት ሰጥተዋል፤ ‹‹ከነበርንበት ችግር ወጥተን ይህን የግብር ንቅናቄ መድረክ ማካሄድ መቻላችን መልካም ነው›› በማለት የአካባቢው እንቅስቃሴ ወደ ሠላማዊ ሁኔታው መመለሡን ገልጸዋል፡፡

በግብር አሰባሰብ ሥርዓቱ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም በዋናነት የንግድ ፈቃድ በየጊዜው የሚቀያይሩ ነጋዴዎች መኖርና ኮንትሮባንድ ንግድ ተጠቅሰዋል፡፡
የኮንትሮባንድ ንግድን በመከላከል፣ ለሚገዙ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ደረሰኝ የመስጠትና የመጠየቅ ልምድን ማዳበር፣ ተገቢ የሆነ የግብር አሰባሰብ ሥርዓትን በመከተል እና ግብር የሚያጭበረብሩትን በማጋለጥ ከችግሩ መውጣት እንደሚቻልም በመድረኩ ተመላክቷል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳንኤል ወርቄ -ከገንዳ ውኃ

Previous articleዘመናዊነት በኢትዮጵያ ከየት ወደ የት?
Next articleበኩር ጋዜጣ ታኅሳስ 20-2012 ዓ/ም