“የኃይል አቀርቦት ችግር ለቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ማነቆ ኾኖበታል” አቶ ዳኛቸው አስረስ

57

ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኃይል አቅርቦት ችግር ተስፋ የተጣለበትን ኢንዱስትሪ ፓርክ አንቆ ይዞታል፡፡ በርካታ ባለሀብቶችም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ገብተው እንዳያለሙ የኃይል አቅርቦት ችግር እንቅፋት ኾኖባቸዋል፡፡ የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክን የኃይል አቅርቦት ችግር ይፈታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክትም በተፈለገው ልክ አልኾነም፡፡

የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ ዳኛቸው አስረስ በቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመብራት ኃይል ችግር ፈተና መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ የኃይል አቅርቦት ችግሩ ባለሀብቶች በሚፈለገው ልክ ገብተው እንዳያመርቱ እንዳደረጋቸውም ገልጸዋል፡፡ የኃይል አቅርቦት ችግሩ እስኪፈታ ድረስ የሚጠብቁ ባለሀብቶች እንዳሉም አንስተዋል፡፡ የኃይል አቅርቦት ችግር ባለሀብት እንዳይገባ፣ የገቡትም በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት እንዳይሸጋገሩ አድርጓቸዋልም ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኩን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት የፓዎር ሳብስቴሽን ግንባታ እና የመስመር ዝርጋታ የማድረግ ሥራዎች መጀመራቸውንም አስታውሰዋል፡፡

የኃይል አቅርቦት ችግሮቹን ለመፍታት ተስፋ የተጣለባቸው ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደያዙትም ነው የገለጹት፡፡ ፕሮጀክቶቹ ከውጭ በሚገቡ እቃዎች ችግር እና በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ግንባታ ማቆማቸውንም ገልጸዋል፡፡

ተቋራጮቹ የውጭ ምንዛሬ ከተፈቀደ ወደ ሥራ እንደሚመለሱና የውጭ ምንዛሬ ካልተፈቀደ ግን ሥራውን እንደማይጀምሩ ገልጸዋልም ብለዋል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ መቆም ምክንያት የኾኑ ችግሮች በአፋጣኝ ሊፈቱ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

አቶ ዳኛቸው የኃይል አቅርቦት ችግሩ ተጨማሪ ባለሀብቶችን ወደ ፓርኩ እንዳይሳቡና መሥራት የሚገባቸውን በጊዜው እንዳይሠሩ እንቅፋት እንደፈጠረባቸውም ገልጸዋል፡፡

የኃይል አቅርቦቱ ችግር ተፈትቶ በመጀመሪያው ምዕራፍ እንዲገቡ የሚፈለጉት ባለሀብቶች ቢገቡና ሙሉ ለሙሉ ወደ ምርት ቢገቡ ለሀገር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ የሀገር እድገት እንዲረጋገጥ መንግሥት ፓርኩ ያጋጠመውን ችግር መፍታት እንደሚገባውም አንስተዋል፡፡ ችግሮቹ ከተፈቱ ለሀገር ከፍተኛ ጥቅሞችን ይዞ እንደሚመጣም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች ላይ ያለውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ያለው የኃይል አቅርቦት በጣም የተወሰነና ፋብሪካዎች የሚፈልጉትን ኃይል ማቅረብ የማይችል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኩን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት ተቋራጭ ተለይቶ ሥራዎች መጀመራቸውንም አንስተዋል፡፡

ለኃይል ግንባታው የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ እንደሚያስፈልገው የገለፁት ዳይሬክተሩ ምንዛሬውን ለማስፈቀድ ሥራ ከተጀመረ መቆየቱን እና እስካሁን ድረስ አለመፈቀዱንም ገልጸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ ተጠይቆ ከብሔራዊ ባንክ ተራ እየጠበቀ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬው መፈቀድ መዘግየት ሥራውንም እንዳዘገየው ነው የገለፁት፡፡ የውጭ ምንዛሬው እንደተፈቀደ የኃይል አቅርቦት ሥራውም በተባለው ልክ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የውጭ ምንዛሬ ተቋራጮቹ ሳይት ላይ እንዳይሠሩ ቢያደርጋቸውም ሌሎች ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውን ነው ያመላከቱት፡፡ ሥራውን ሙሉ ለሙሉ አቁመዋል ማለት እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬ እንደተፈቀደ ሥራውን በተገቢው መንገድ እንደሚያስቀጥሉም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎበኙ።
Next article“በወቅታዊ ሰላምና የጸጥታ ላይ የጋራ አረዳድ በመፍጠር የተጀመረው የሠላምና የልማት ሂደቱ እንዲጠናከር መሥራት ይገባል” ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)