
ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታዎች ለማድረግ ዛሬ አመሻሹ ላይ አሜሪካ ገብቷል፡፡
በጊዜያዊ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም የሚመሩት ዋልያዎቹ በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት ማረፊያቸውን ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ብሔራዊ ቡድኑ በአሜሪካ ቆይታው ሐምሌ 26 ከጉያና ብሔራዊ ቡድን እና ሐምሌ 29 ከአትላንታ ሮቨርስ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።
ከጉያና ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚደረገው ጨዋታ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የተመዘገበ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።
ቡድኑ ለጨዋታዎቹ ከሐምሌ 13 እስከ 22/2015 በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
በኢንስትራክተር ዳንኤል ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል አራቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውንና ከአትላንታ ሮቨርስ ጋር በሚደረገው ጨዋታ እንደሚሳተፉ ነው ፌዴሬሽኑ ያመለከተው።
የብሔራዊ ቡድኑ የአሜሪካ ጉዞ ስፖርታዊ እና የገበያ (ማርኬቲንግ) ጥቅም ያለው ነው ያለው ፌዴሬሽኑ ቡድኑን አሜሪካ ካለው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር ለማቀራረብ እንደሚያስችልም ጠቅሷል።
በጨዋታዎቹ የኢትዮጵያ ተጫዋቾች በመልማዮች እይታ ውስጥ ገብተው በቀጣይ በተለያዩ ፕሮፌሽናል ክለቦች ለመጫወት በር እንደሚከፍትላቸውም ታምኖበታል።
ሁለቱ ጨዋታዎች በዋሺንግተን ዲሲ እና አትላንታ ይደረጋሉ።
የአሜሪካውን ጉዞ ያሰናዳው ቤይ ማርት የተሰኘ ተቋም ሲሆን ፌዴሬሽኑ እና ተቋሙ የልዑካን ቡድኑን አባላት ወጪ እንደሚሸፍኑ ለማወቅ ተችሏል።
ዋልያዎቹ የአሜሪካ ጉዟቸውን አጠናቀው እስከ ነሐሴ 2/2015 ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!