
ደብረ ብርሃን: ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ወደ ሪጂዮ ፖሊታን ከተማነት ካደገች በኋላ የከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ በአዲስ መንገድ በመደራጀት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው ተብሏል። መምሪያው የ2015 በጀት ዓመት የትግበራ ክንውኑን እየገመገመ ነው።
በግምገማው ላይም የጤና መሠረተ ልማትን በማሳደግ የኀብረተሰብ ጤና ክብካቤ ላይ ሰፊ ሥራ መሠራቱን መምሪያ ኀላፊው በቀለ ገብሬ ተናግረዋል።
በአሥተዳደሩ በሚገኙ ጤና ተቋማት የግብዓት አቅርቦት በማሟላትና ለተገልጋዮች ምቹ ኹኔታን በመፍጠር ረገድ አበረታች ውጤት ታይቷል ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው በከተማዋ እያደገ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ተከትሎ የነዋሪዎችን ጤንነት ለመጠበቅ እየተሠራ ያለው ሥራ መልካም አፈጻጸም የታየበት ስለመኾኑ ተናግረዋል።
በማኀበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ላይ ካሁን በፊት የታየው ዝቅተኛ አፈጻጸም ተሻሽሎ ጠቅላላ ተገልጋዮችን 88 ከመቶ ማድረስ መቻሉ በመልካምነት የሚታይ ስለመኾኑም ተጠቅሷል።
ጤና መምሪያው በክረምት ወቅት በልዩ ትኩረት ከሚሠራቸው ጉዳዮች መካከል የክረምትን መግባት ተከትሎ በሚከሰቱ በሽታዎችና ተያያዥ ጉዳዮችን ጨምሮ የ2016 ቁልፍ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፡- ኤልያስ ፈጠነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!