
ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ለሀገር እድገት ከፍተኛ ተስፋ የተጣለባቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተዋል፡፡ ከፍተኛ ተስፋ ከተጣለባቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪያል ፓርክ አንደኛው ነው፡፡ ፓርኩ በሦስት ምዕራፎች ይገነባል፡፡ የፓርኩ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቅቆ ክፍት ከኾነ ቆይቷል፡፡
ባለሀብቶችም ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በመግባት እንዲያለሙ ጥሪ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ ወደ ቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክም በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ያስመዘገቡ ባለሀብቶች እየገቡ ነው፡፡
የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሥራ አሥኪያጅ ዳኛቸው አስረስ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ያስመዘገቡ 37 ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ ወደ ኢንዱስትሪያል ፓርኩ የገቡ ባለሀብቶች 102 ሄክታር የለማ መሬት መረከባቸውንም ተናግረዋል፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ ይለማል ተብሎ ከታሰበው መሬት አብዛኛው ለባለሀብቶች መተላለፉንም ነው የገለጹት፡፡ የውጭ ሀገርና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፕሮጄክት ቀርጸው እያስገቡ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ወደ ፓርኩ ለመግባት ያለው ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት በርካታ ከፍተኛ ሀብት ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ እንደሚገቡ ይጠበቃል ነው የተባለው፡፡
ክልሉ በአስቸጋሪ ሂደቶች ውስጥ እንዳለፈ ያነሱት ሥራ አሥኪያጁ ችግሮች ቢኖሩም የክልሉ መንግሥት ባለሀብቶች እንዲገቡ እያደረገው ያለው ጥረት እና የባለሀብቶችም ፍላጎት የሚበረታታ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በመጀመሪያው ምዕራፍ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ገብተው እንዲያለሙ የሚፈለጉት ባለሀብቶች ሙሉ ለሙሉ እንደሚገቡ ይጠበቅ እንደነበር ያነሱት ሥራ አሥኪያጁ የነበረው የጸጥታ ችግር በሚፈለገው ፍጥነት አለመሳካቱንም ነው የተናገሩት፡፡ አሁን ከገቡት ባለሀብቶች የበለጠ ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ እንዲገቡ እንደሚጠበቅም አንስተዋል፡፡ አሁን ላይ የገቡት ባለሀብቶችም በቀላል የሚታዩ አለመኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከገቡ ባለሀብቶች መካከል ወደ ምርት የገቡ መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ለሀገር የውጭ ምንዛሬ እያመጡ ያሉና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ እንዳሉም አንስተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ፓርኩ የሚፈለገውን ዓላማ እንዲያሳካ በትኩረት እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ለዋናው ፓርክ መጋቢ የኾኑ ቅርንጫፎች ሥራቸው እየተጠናቀቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ለመግባት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!