
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 19/2012ዓ.ም (አብመድ) ዘመናዊነት በራሱ አከራካሪ ሐሳብ ነው፡፡ ዘመናዊነት የበለጠ የሰውን ልጅ ነፃ ያወጣዋል ወይስ ጦርነትን እና እልቂትን ያባብሳል? የሚለው ጥያቄም እስካሁን ድረስ በዘርፉ ምሁራን ዘንድ ወጥ የሆነ ምላሽ አላገኘም፡፡
የዘመናዊነት ሐሳብ በኢትዮጵያ ‹‹ከምዕራባውያን ዓለም የትምህርት ሥርዓት መስፋፋት፣ ከሀገር በቀል ባህል ትችት እና በዘውዳዊው ሥርዓት እና በምዕራባውያን አመለካከት መካከል ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተነጣጥሎ መታየት አይችልም›› የሚሉ ምሁራን በርካቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም ‹‹ዘመናዊነት በኢትዮጵያ ውስጥ በተስፋፋ ቁጥር የዕውቀት ማዕከላት የነበሩት የሃይማኖት ተቋማት በዘመናዊ ትምህርት ቤቶች መተካት ጀመሩ›› የሚሉን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ምሁሩ ፋሲል መራዊ ናቸው፡፡ ‹‹ስልጣኔ ማለት ዘመናዊ ተቋማት፣ ዘመናዊ ትምህርት እና ዘመናዊ አስተሳሰብ ማለት ሆነ›› ይሉናል፡፡
የፍልስፍና ምሁሩ በተጨማሪም ‹‹የዓፄ ቴዎድሮስ የመንግሥት ምሥረታ እና ማዕከላዊ የሆነ አስተዳደር የዘመናዊነት ግቦች በኢትዮጵያ እንዴት ከሃይማኖት፣ ወግና ባህል ጋር እንደተጋጩ ያሳየናል›› ብለዋል፡፡ የዘርዓ ያዕቆብን ‹‹ሐተታ›› ዋቢ አድርገውም ‹‹በፍልስፍናዊ አመለካከቱ ውስጥ የወግ፣ የባህል እና የሃይማኖት ትችቶች እናገኛለን›› ብለው አብነት ጠቅሰዋል፡፡ እንደ አቶ ፋሲል ፍልስፍና በተፈጥሮው የነገሮችን መሠረት በመመርመር እና በመጠየቅ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የግብረ ገብ አስተምህሮ እና ምክንያታዊ የተፈጥሮ ሕግጋት መካከል ቁርኝት እንዳለም አመላካች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የምዕራባውያኑ ዓለም ዘመናዊነት ከሰው ልጅ የተለየ እና ዳር ተቁሞ የሚጠና የነገሮች ስብስብ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ዓለም ዘመናዊነት ደግሞ ሰዎች ራሳቸው በጥብቅ የሚቆራኙበትና በሂደትም የራሳቸውን አስተዋፅኦ እና ድጋፍ የሚያደርጉበት ሰዋዊ ዓለም ነው፡፡ ስለዚህም ይላሉ የፍልስፍና ምሁሩ ‹‹የምዕራባውያን ስልጣኔ ከሀገር በቀል ባህል ጋር መዛመድ ይኖርበታል፡፡ የአንድ ማኅበረሰባዊ ዘመናዊ ዕድገት በሰዎች እኩልነት፣ ምክንያታዊነት እና ማኅበረሰባዊ ፍትሕ ላይ መታነፅም ይኖርበታል›› ባይ ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ሳምነር ‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና› በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹ኢትዮጵያውያን ባህላቸውን እና ወጋቸውን ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩት ከውጪ ንክኪ በመጠበቅ ሳይሆን ማንኛውንም ከውጪ የሚመጣን ዘመናዊ ሐሳብ ወደ ራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ የማዋሐድ ብልሃት እና ልምድ ስላላቸው ነው›› ብለዋል፡፡ በዘመናዊው እና የእርስ በእርስ መስተጋብሩ በጠበቀበት ዓለም ውስጥ ኢትዮጵያውያን አብረው በመቻቻል መኖር የሚችሉበትን እሴቶች መፈለግ እና ማዳበር ይኖርባቸዋል፡፡
በግጭት ወቅት ‹‹አቆራኙኝ›› በማለት በሕግ ልዕልና የሚያምን፣ ‹‹በፍትሕ ከሄደችው በቅሎየ ያለፍትሕ የሄደችው ጭብጦየ ይበልጥ ታመኛለች›› የሚል ፍትሕ አዋቂ ሕዝብ እና ‹‹እንኳን ሰው ዛፍ ያስጥላል›› የሚል የይቅርታ እና ሽምግልና እሴቶች ባለቤት የሆነ ማኅበረሰብ የራሱን ሀገር በቀል ወግ፣ ባህል እና እሳቤ ከማዳበር የዘለለ ዘመናዊነት ሊኖር አይችልም፡፡ ‹‹ይህን ይበልጥ ለማዳበር የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር በጣም የዳበረ የዘመናዊነት ዲስኩር እንዲኖረን ተደጋጋሚ ውይይቶች ብቻ በቂ ናቸው›› ብለዋል አቶ ፋሲል፡፡
የፍልስፍና ምሁሩ በመጨረሻም የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ጉዞ ከነበረው ሀገር በቀል የአስተሳሰብ እርሾ ላይ በመጨመር እንጂ የነበረውን አጥፍቶ በአዲስ በመተካት ላይ መመሥረት እንደለሌበትም ምክረ ሐሳብ ያስቀምጣሉ፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው