በክልሉ በዘር ከተሸፈነው ሰብል ውስጥ 90 በመቶ የሚኾነው የእንክብካቤ ሥራ እንደተሠራ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

57

ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ እንዳሉት በዚህ ዓመት ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ነበር ወደ ሥራ የተገባው፡፡
በመኸር እርሻ ሥራ ከ160 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘትም ታቅዶ እየተሠራ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ሂደት ሰፊ የዝግጅት ምዕራፍ ሲካሄድ ቆይቶ ነው ወደ ተግባሩ የተገባው ብለዋል የሰብል ልማት ጥበቃ ዳይሬክተሩ፡፡

የአንደኛ የመኸር እርሻ በክልሉ ከታቀደው በላይ መሠራቱንም ለአሚኮ አረጋግጠዋል፡፡

ለዚህም ዋና ምክንያቱን ሲያብራሩ እንዳሉት በዚህ ዓመት ዝናቡ ቀድሞ መግባት መቻሉ እና በስርጭትም በመጠንም ካለፈው ዓመት የተሻለ ነበር ብለዋል፡፡

ለአገዳ ሰብሎች፣ ለብዕር ሰብሎች እና ለእርሻ ሥራ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አስገንዝበዋል፡፡

የዘር ኹኔታውን አስመልክተው ዳይሬክተሩ ሲያብራሩ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል፡፡

በዘር የተሸፈነው በቆሎ፣ ማሽላ እና መሰል ሰብሎች በጥሩ ኹኔታ ላይ እንደሚገኙም ነው ያብራሩት፡፡

አርሶ አደሮች ወደ ጤፍ እና ስንዴ ዘር ሲገቡ መዘናጋት እንዳይኖር የአረም እና የተባይ አሰሳ ቁጥጥሩን በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡

በክልሉ ከ600 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ እንደተሸፈነ የገለጹት ዳይሬክተሩ ከ90 በመቶ በላይ የአረም ሥራው መከናወኑንም ገልጸዋል፡፡

የተባይ አሰሳውም እየተሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ አግደው በመጀመሪያ በዝናቡ ወጣ ገባነት ምክንያት የተከሰተው የተባይ ኹኔታ አሁን ዝናቡ ሲስተካከል መጥፋቱን አስረድተዋል፡፡

አሁንም ቢኾን ግን ዝናቡ ወጣ ገባ በኾነባቸው ምዕራብ አርማጭሆ በለሳ፣ ወልቃይት እና መሰል አካባቢዎች የተባይ ሁኔታ መከሰት ይሰተዋላል ነው ያሉት፡፡

የአረም ሥራው እንደየ አካባቢዎቹ የሚለያይ እንደኾነ የነገሩን አቶ አግደው አንዳንድ አካባቢዎች እስከ ሦስተኛ ዙር የበቆሎ እና መሰል ሰብሎች አረም ያከናወኑ ስለመኖራቸው እና የተሻለ የሰብል እንክብካቤ በክልሉ እንዳለ ነው የጠቆሙት፡፡

ዳይሬክተሩ ሁሉም በዘር ያልተሸፈኑ መሬቶች በዘር እንዲሸፈኑ አሳስበው የአረም እና የተባይ ቁጥጥሩም ከመቸውም ጊዜ በላይ ትኩረት በመስጠት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለተማራችሁበት እና ላስተማራችሁበት ትምህርት ቤት ያደረጋችሁት እንቅስቃሴ ከትምህርት ቤቱ ባሻገር የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻነት የሚያጎለብት ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።