“ለተማራችሁበት እና ላስተማራችሁበት ትምህርት ቤት ያደረጋችሁት እንቅስቃሴ ከትምህርት ቤቱ ባሻገር የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻነት የሚያጎለብት ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)

49

ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞው የጣና ሐይቅ አጠቃላይ ከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና መምህራን በትምህርት ቤቱ ቀጣይ እጣ ፋንታ ላይ እየመከሩ ነው።
መምህራኑ በ1970፣ 80 እና 90 ዎቹ ላይ ተማሪ እና መምህር የነበሩ ናቸው።

የጣና ሐይቅ አጠቃላይ ከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1957 ዓ.ም አፄ ሠርፀ ድንግል አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚል ስም ይጠራ እንደነበረ መረጃው ያሳያል።
ትምህርት ቤቱ በወቅቱ በ12 መምህራን እና በ120 ተማሪዎች ሥራ የጀመረ ሲኾን አሁን ላይ ከ3 ሺህ 853 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ነው።

የጣና ሐይቅ ትምህርት ቤት በአንድ ጊዜ እዚህ ደረጃ እንዳልደረሰ የተናገሩት የአሁኑ ርእሰ መምህር ሙጬ ባሳዝነው ናቸው።
ትምህርት ቤቱ እድሜ ጠገብ ይሁን እንጂ በበርካታ ውጣ ውረዶች አልፎ ለዚህ መብቃቱን እና አሁንም በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቱ ለ53ኛ ጊዜ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ያስፈተነ ሲኾን በትምህርት ቤቱ የተማሩ ተማሪዎች በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተሠማርተው እየሠሩ መኾኑን የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ የሙያ ትምህርቶች ይሠጡበት እንደነበርም ርእሰ መምህሩ አንስተዋል።

ትምህርት ቤቱ የታለመለትን ዓላማ ያሳካ ዘንድ ዛሬ በስሙ የተሠበሰቡ የቀድሞ መምህራን እና ተማሪዎች ሌሎችን በማስተባበር የድርሻቸውን ይወጡ ዘንድ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ትምህርት ቤቱ ዛሬም ያልተጠገኑ መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጽሐፍት እና ሌሎችም ክፍሎች እንዳሉት ያነሱት ርእሰ መምህሩ በቀጣይ በርካታ ሥራ መሠራት እንዳለበት አንስተዋል።

የ70፣ 80፣ 90ዎቹ ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሮ ትዕግስት ንጉሡ ዓላማው ውቢቷ ባሕር ዳርን ለዓለሙ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ እና የጣና ሐይቅ አጠቃላይ ከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ለማገዝ እንደኾነ ጠቅሰዋል።
የባሕዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) በትምህርት ዓለም ያለፈ ሰው ለትምህርት ትልቅ ዋጋ ይሠጣል ብለዋል።

“ለተማራችሁበት እና ላስተማራችሁበት ትምህርት ቤት ዋጋ ሠጥታችሁ ያደረጋችሁት እንቅስቃሴ ከትምህርት ቤቱ ባሻገር የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻነት የሚያጎለብት በመኾኑ አጠናክረን እናስቀጥላለን” ብለዋል።
መንግሥትም ጉዳዩን እንደሚደግፍ ስንገናኝ የምናወራው ትዝብታችን ብቻ ሳይኾን ቀጣይ መዳረሻዋ ላይ የሚታይ እና የሚነሳ ሀሳብ እንደኾነ አስረድተዋል።

ይኽን ሀሳብ ላነሱ አካላት ምሥጋናም አቅርበዋል። ሀሳቡን ለሌሎች በማካፈል የክልሉን ችግር የምንቀርፍበት ይኾናልም ነው ያሉት።

የተጀመረው መንገድ ሁሌም የልብ ትስስርን የሚፈጥር አንድነትን እና ኅብረትን የሚያመጣ ሀሳብ ነው ያሉት ዶክተር ድረስ ሌሎች ችግሮችን በአንድነት እና በጋራ መቅረፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ፕሮግራሙ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲኾን በዚህ ሳምንት ለሰባት ቀን የሚቆይ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች መኖራቸውን ከአስተባባሪዎች ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሞጣ ከተማ አሥተዳደር ከ102 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።
Next articleበክልሉ በዘር ከተሸፈነው ሰብል ውስጥ 90 በመቶ የሚኾነው የእንክብካቤ ሥራ እንደተሠራ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡