
ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሞጣ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ገዳሙ መኮነን ፕሮጀክቶቹ የተገነቡት ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ፣ በክልሉ መንግሥት ድጎማ፣ ከከተማ አሥተዳደሩ የውስጥ ገቢና ከማኀበረሰብ ተሳትፎ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ መኾኑን ተናግረዋል።
ተመርቀው አገልግሎት መሥጠት የጀመሩት ፕሮጀክቶች በአንድ ጊዜ ከ350 መኪና በላይ ማስተናገድ የሚችል የመኪና መናሃሪያ ፣ የውስጥ ለውስጥ የጠጠር መንገድ ፣ የጎርፍ መፋሰሻ ዲች፣ የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ፣ ድልድይ፣ የሰባቱ ዋርካ መዝናኛ ማዕከልን ጨምሮ በአጠቃላይ 43 ፕሮጀክቶች መኾናቸውን ከንቲባው ተናግረዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ ሰብለወንጌል ዳኜ በከተሞች ኀብረተሰቡ ሊሳተፍባቸው በሚገቡ የማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ሥራዎች ላይ ሕዝቡ በገንዘብ፣ በጉልበትና በአይነት የሚያደርገው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱም ከ125 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።
በዞኑ የዓለም ባንክ ድጋፍ የመሰረተ ልማት ሥራዋች የእቅዱን 98 ነጥብ 7 በመቶ ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ ተችሏል። ከዓለም ባንክ ውጭ የኾኑ ከተሞች ፕሮጀክት ብዛት 104 ሲኾኑ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ቢያዝን እንኳኾነ የክልሉ መንግሥት ከተሞችን በመሰረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።
የማኀበረሰቡ ድርሻ እያደገ ስለመማጣቱ የተናገሩት ኀላፊው ማኀበረሰቡም ፕሮጀክቶቹን በባለቤትነት ስሜት እንዲጠቀምባቸው አሳስበዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች የፕሮጀክቶች መመረቅ ደስታን እንደፈጠረላቸው እና በክረምት ወቅት ይደርስባቸው ከነበረው እንግልት እንደታደጋቸዉ ተናግረዋል። የተገነቡ መሰረተ ልማቶቹን በኀላፊነት እንደሚጠቀሙባቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ንጉስ ድረስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!