
አዲስ አበባ: ሐምሌ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 4ኛው የኢትዮ- ደቡብ አፍሪካ ሚኒስትሮች የጋራ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በጉባኤው የሁለቱን ሀገራት የቆየና ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክርና ድህነትን በጋራ ለመዋጋት የሚያስችል የፊርማ ሥነ ሥርዓትም አካሂደዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በየጊዜው የሚደረጉ የሁለትዮሽ የፊርማ ሥነ ሥርዓቶች የሀገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክሩ በመኾናቸው ተፈጻሚነታቸውን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች መከታተል አለብን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚገኙ በመኾናቸው የአፍሪካን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለማስመለስ በጋራ ሊሠሩ ይገባል ያሉት ደግሞ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓናዶር (ዶ.ር) ናቸው።
በጉባኤውም በሁለቱ ሀገራት የፀጥታ፣ የኢኮኖሚ፣ የፓለቲካ እና የማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!