“አልማ ኀብረተሰብን በማሳተፍ በውስን ሀብት ጥራት ያላቸው ግንባታዎችን መሥራት እንደሚቻል አሳይቶናል” አቶ በድሉ ውብሸት

34

ደብረ ብርሃን: ሐምሌ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን አልማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በእምዬ ምንሊክ ክፍለ ከተማ ስር ለሚገኘው የደሊላ ቀበሌ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደረጃውን የጠበቀ ቤተ መጽሐፍት አስገንብቶ አስመርቋል::
ግንባታው በ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ስለመከናወኑ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ አባተ አውግቸው ተናግረዋል::

ኀላፊው ኀብረተሰቡ ኘሮጀክቱን በገንዘብና በጉልበት ከመደገፉም ባሻገር በባለቤትነት ግንባታውን በቅርበት በመከታተል በጥራት እንዲጠናቀቅ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል::

በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የከተማ አሥተዳደሩ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት አልማ ኀብረተሰብን በማሳተፍ በውስን ሀብት ጥራት ያላቸው ግንባታዎችን መሥራት እንደሚቻል አሳይቶናል ብለዋል::

ለቤተ መጽሐፍቱ የሚያስፈልጉ መጽሐፍትና ሌሎች ግብአቶችን በአጭር ጊዜ ለማሟላት እንደሚሠራም ገልጸዋል::

ክልላችን ባለፉት ዓመታት ባለመረጋጋት ውስጥ ቢኾንም አልማ በእነዚህ ወቅቶች ጭምር የኀብረተሰቡን የመልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመሥጠት እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች ቀላል የማይባሉ ናቸው ብለዋል አቶ በድሉ።

ኀብረተሰቡ ከመቸውም ጊዜ በላይ የአልማ አባልነቱንና ተሳትፎውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉት ምክትል ከንቲባው ከተማ አሥተዳደሩም ጠንካራ የአልማ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ከአልማ ጎን ኾኖ በቅንጅት ይሠራል ብለዋል::

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው አስተያየታቸውን የሰጡ የቀበሌው ነዋሪዎች አልማ በቀበሌው ባስገነባው ቤተ መጽሐፍት መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይም አባልነታችንን በማጠናከር ከአልማ ጎን እንቆማለን ብለዋል::

ዘጋቢ ፡- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በመምሪያው ግቢ የሚገኘውን መሬት አትክልት አልምተን ተጠቃሚ ኾነናል” የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ሠራተኞች
Next article“ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለማስመለስ በጋራ ሊሠሩ ይገባል።” የኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች