
ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም እንዲችሉና የተመጣጠነ ምግብ ያገኙ ዘንድ አነስተኛ ገቢ ላላቸው 23 ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞቹ በግቢው ያለውን መሬት አልምተው እንዲጠቀሙ አድርጓል፡፡
አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች መሰል ድጋፍ ማድረግ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ የመተዛዘንን እና የመረዳዳትን ባሕል ስለሚያጠናክር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገልጿል፡፡
ሠራተኞቹ ካለፈው ዓመት ጀምሮ አትክልቶችን አልምተው መጠቀም ጀምረዋል። ዘንድሮም የዘር፣ የማዳበሪያና የሙያ እገዛ ተደርጎላቸው ገቢ የሚያስገኙ የአትክልት ልማት እየሠሩ ነው፡፡
አትክልት አልምተው ከሚጠቀሙ ሠራተኞች መካከል ወይዘሮ አለምነሽ እሸቴና አቶ አምሳሉ ጌትነት ባለፈው ዓመት ጀምረው ማልማታቸውንና ጥቅም ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህም ድጋፍ ሰጪ ሠራተኛውን እንዳበረታታው አስረድተዋል፡፡ ሠራተኞቹ በተደረገላቸው ድጋፍ ተጠቃሚ መኾናቸውንም ገልጸው አመሥግነዋል፡፡
በመምሪያው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ቡድን መሪ አቶ ለጋስ ጀንበር ለሠራተኞቹ ሥልጠና፣ የአትክልት ዘርና በሥራቸው ላይም ተግባራዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ለሠራተኞቹ የተደረገው ድጋፍ ለራሳቸውም ለመምሪያውም ሠራተኛ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ ማድረጉንም ነው አቶ ለጋስ የተናገሩት፡፡
የመምሪያው ኀላፊ አዲስ ተፈራ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሠራተኞች የተደረገው እገዛ ሠራተኞቹን በኢኮኖሚ ለማገዝ እንደሚጠቅም አስረድተዋል፡፡
አቶ አዲስ ሌሎች ተቋማትም በክልሉ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሠራተኞች ለማገዝ ተመሳሳይ ሥራ መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በዞኑ ሥር የሚገኙ የወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤቶችም ይህንኑ ተግባር እንዲፈጽሙ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!