
ደባርቅ: ሐምሌ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ከደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ጋር በመተባበር ለ 12 ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተመደቡለትን ፈታኞችና አስተባባሪዎች የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን አስጎብኝቷል።ፈታኞቹ የመጀመሪያውን ዙር ፈተና ፈትነው ካጠናቀቁ በኋላ ነው ጉብኝቱን ያደረጉት።ጭልቋኒት፣ጨነቅና ቧሂት የሚባሉ የፓርኩን ዋና ዋና ክፍሎችም ጎብኝተዋል።
ያነጋገርናቸው ፈታኝ መምህራን ባለፈው ዓመት በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ከፈተኑ መምህራኖች ባገኙት መረጃ ተማምነው መምጣታቸውን ተናግረዋል። ደባርቅ ፍጹም ሰላም፤ማኅበረሰቡም ፍጹም ሰላማዊ ሕዝብ መኾኑ በቆይታችን አረጋግጠናል ነው ያሉት።
ማኅበረሰቡ እንግዳ ተቀባይና ሰው አክባሪ መኾኑን ነው የተረዳን ብለዋል። ሥለኾነም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሳሳተ መረጃ በመልቀቅ የሕዝብ እሴት የሚያጎድፉና ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚጥሩ አካላት ሊታረሙ ይገባል ብለዋል።
ፈታኞቹ በቴሌቪዥን መስኮት ይመለከቱትና በአካል ለማየት ይመኙት የነበረውን የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን በማየታቸው ደስተኞች መኾናቸውንም ተናግረዋል።
በሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጉብኝታቸው ከውብ መልክዓምድሩ በተጨማሪ ጭላዳ ባቡን፣ዋልያና መሰል ብርቅዬ እንሰሳትን ማየት የቻሉት ፈታኞቹ “ሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊጎበኘው የሚገባ ድንቅ መልክዓምድር ነው” ብለዋል።
ፈታኞቹ ጉብኝቱን ላመቻቹት የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ እና ደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ምሥጋና አቅርበዋል።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀጃው ደማሙ (ዶ.ር) የ 12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በዩኒቨርሲቲ መሰጠቱ ኩረጃን በመከላከል የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ ባለፈ ፈታኞች ሀገራቸውን እንዲያውቁ፣ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ በመኾናቸውም የማኅበረሰብ መልካም መስተጋብር እንዲፈጠር ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
ፈታኞች በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ፣ደባርቅ ከተማና ሰሜን ተራራዎች ፓርክ ቆይታቸው የተመለከቷቸውን ነገሮች ለሚሄዱበት ማኅበረሰብ በማሳወቅ የአካባቢውንም የማኅበረሰቡምን ገጽታ ይገነባሉ ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀጃው ፈታኞች ሀገር አቆራርጠውና ውጣ ወረዱን ተቋቁመው ሀገራዊ ተልዕኮውን ለማሳካት ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ዘጋቢ:-አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!