
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 19/2012ዓ.ም (አብመድ) የከተማ አስተዳደሩ ደግሞ ኅብረተሰቡንና የፀጥታ አካሉን በማቀናጀት ውጤታማ የሆነ ሥራ እየሠራ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ያነጋራቸው ነዋሪዎች ምሽት ላይ የሰሌዳ ቁጥር የሚንቀሳቀሱ ባለሦስት እግር (ባጃጅ) ተሽከርካሪዎች ለስርቆት ተግባር እየዋሉ ነው፡፡ አሽከርካሪዎቹ በኮንትራት ወይም በታሪፍ ከጫኑ በኋላ ተሳፋሪ አስመስለው ከሚጭኗቸው ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የዝርፊያ ወንጀል እንደሚሠሩ ነው ነዋሪዎች የተናሩት፡፡ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ደግሞ በምሽት ብቻውን በሚጓዝ ሰው ላይ ተከትለው ጥቃት እንደሚያደርሱ አስተያዬት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል፡፡ የመንገድ ላይ መብራት በማይበራባቸው እና ሰው በማይበዛባቸው ጎዳናዎች ላይ ዝርፊያ እንደሚዘወተርም አመልተዋል፡፡
እኛም በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክና በጣና ሐይቅ ክፍለ ከተሞች ባደረግነው ቅኝት የምሽት ላይ ስርቆትንና ዝርፊያን ለመከላከል ነዋሪዎቹ በጋራ የቀጠሯቸውን ጥበቃ ሠራተኞች ተመልክተናል፡፡ ጥበቃ በተቀጠረባቸው ክፍለ ከተሞች ሲደርስ የነበረውን ዝርፊያና ስርቆት ማስቆም እንደተቻለም ተነግሮናል፡፡ ነዋሪዎቹ የከተማ አስተዳደሩ የፀጥታ ኃይል ከስጋት ነጻ እንዲያደርጋቸውም ጠይቀዋል፡፡ እንደ አስያዬት ሰጪዎቹ በጥቂት ሰዎች የሚፈጸመው የወንጀል ድርጊት ንጹኃን የከተማዋን ነዋሪ ስም እያጠለሸ ነው፡፡ ወደ ከተማዋ ሚመጣ ጎብኚ ላይም ስጋት የሚፈጥር ሆኗል፡፡ በመሆኑም አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የሠላምና ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ ዘውዱ ዘለቀ የከተማዋ ነዋሪዎችም ሆኑ ጎብኚዎች ያለምንም ስጋት እንዲንቀሳቀሱ የፀጥታ ኃይሉ በቅንጅት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተለይም ባጃጅ ስምሪት ውስጥ ገብቶ መሥራት ከጀመረ ወዲህ ለኅብረተሰቡ የማይመቹ ድርጊቶች መኖራቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአሽከርካሪም ይሁን በእግር እየተንቀሳቀሱ ከማኅበረሰቡ ባህልና እሴት የወጣ ተግባር የሚፈጽሙ አካላትን ለመከላከል የፀጥታ ኃይሉ ከመቼውም በበለጠ በቅንጅት እየሠራ ነው›› ብለዋል መምሪያ ኃላፊው፡፡ በከተማ የፀጥታ ኃይሉን ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን ባለቤት በማድረግ እስከ ‹ብሎክ› ድረስ የሚደርስ ቅንጅት እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡
‹‹የባሕር ዳር ከተማ ወጣት በከተማዋ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር መከሰት የለበትም ብሎ የሚያምን ነው›› ያሉት ኃላፊው 10 የሚደርሱ ሠላምና ፀጥታን በማስከበር የተደራጁ የወጣት አደረጃጀቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ የወጣት አደረጃጀቱ በከተመዋ ከሚንቀሳቀሰው የፀጥታ ኃይል ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑንና መልካም ውጤት እየተመዘገበ እንደሆነም አስውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ