በዓለም በየቀኑ ከ800 በላይ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ያልፋል፤ ከእነዚህ ውስጥ 59 በመቶ የሚሆኑት ለሞት የሚዳረጉት ግጭት በሚያስከትለው ዳፋ ነው፡፡

166

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 19/2012ዓ.ም (አብመድ) ኪነ-ጥበብ ለእናቶችና ለሕጻናት ማኅበር በባሕር ዳር ከተማ “ሠላም ለእናቶች እና ለሕጻናት” በሚል መሪ ሐሳብ የኪነ-ጥበብ መድረክ አካሂዷል። ትናንት ምሽት በሙሉዓለም የባህል ማዕከል የተካሄደው የኪነ ጥብብ መድረክ የተዘጋጀበት ዋነኛ ዓላማም በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ በሚፈጠሩ ግጭቶች እናቶች እና ሕጻናት ከፍተኛ ሠለባ መሆናቸውን በማስገንዘብ ሁሉም አካል ለሠላም ዘብ እንዲቆም ለማሳሰብ ነው።

የኪነ-ጥበብ ለእናቶችና ለሕጻናት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ እና አዋላጅ ነርስ ፈንታሁን ፈቃዴ እንዳሉት በሀገሪቱ የሚነሱ ጥያቄዎች አቀራረባቸው በተሳሳተ መልኩ በመሆኑ የእርስ በእርስ ግጭቶች ተፈጥረዋል። “በዚህ ጊዜ ግጭት የፈጠሩ አካላት ጎራቸውን ይዘው ይፋለማሉ፤ አለበለዚያም ያፋልማሉ፡፡ እናቶች እና ሕጻናት ግን ማምለጫ አጥተው ሰለባ ይሆናሉ። እኛ እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ የምናደርገው ልጅም እናትም ጤናማ እንዲሆኑ ነው። ታዲያ አንዳንዶች በሚፈጥሩት ግጭት ተሰቃይተው የሚሞቱ ከሆነ እኛ ለምን እንለፋለን?” በማለት ለኪነ-ጥበብ መድረኩ ታዳሚዎች ጠይቀዋል።

“የኪነ ጥበብ መድረኩ ዋና ዓላማ መቶ ጊዜ ለክቶ አንድ ጊዜ መቁረጥን ለማሳሰብ ነው” በማለትም ሁሉም አካላት ለሠላም ዘብ እንዲቆሙ አሳስበዋል፤ ግጭት ወደሚፈጥሩ ተግባራት ከመግባት በፊት የሚያስከትሉትን አደጋ ደጋግሞ መመርመር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በዓለም በየቀኑ ከ8 መቶ በላይ እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል። ከነዚህ መካከል ደግሞ 59 በመቶ የሚሆኑት ከሠላም መደፍረስ ጋር በተያያዘ ጭንቀት በሚከሰት ያልተጠበቀ ምጥ እና ተያያዥ ምክንያቶች የሚሞቱ ናቸው።

ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆነ 250 ሚሊዮን ሕጻናት ደግሞ ግጭት በሞላባቸው ሀገራት ይኖራሉ። ይህም ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እጥፍ በላይ እንደማለት ነው። ግጭት የአንድን ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መስተጋብር ያዛባል፣ በተለይም በእናቶች እና ሕጻናት ላይ የሚያደርሰው የሕይወት መጥፋት እንዲሁም አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫና በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። በመሆኑም ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ግጭትና ሁከትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን ለመፈጸም ሲነሳሳ እናቱ፣ እህቱ፣ ልጁ ወይንም የትዳር አጋሩ የግጭቱ ዋንኛ ሰለባ መሆናቸውን በአዕምሮው ማሰብ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

በተለይም ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል በርካታ ጥያቄዎች ሊኖሩት ቢችሉም ጥያቄዎቹን በሠላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ የሠለጠነ አካሄድን እንዲከተል አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleበዋሽንግተን ዲሲ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አደረጃጀት ነገ ይቋቋማል፡፡
Next articleባሕር ዳር በተሽከርካሪ የሚፈጸም ስርቆት እና ዝርፊያ እንዲቆም ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡