“ሕዝብን ለማገልገል የሥራ ድንበር የለውም” ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር)

57

👉በፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር በ157 ሚለዮን ብር የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ተመርቀዋል።

ፍኖተ ሰላም : ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የንግድና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ዴእታ እንዳለው መኮንን፣ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳደሪ መልካሙ ተሾመ፣ የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ልየው አንሙትን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ልየው አንሙት ፍኖተ ሰላም ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ያረፉባት፣ የተለያዩ እንግዶች የሚያርፉባት፣ እንደ ስሟ የሰላም መንገድ የኾነች ናት ብለዋል። ፍኖተ ሰላም ለንግድና ለኢንቨስትመንት ምቹና ተስማሚ መኾኗንም ተናግረዋል። በከተማዋ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ያነሱት ከንቲባው አሁንም በከተማዋ ሥራ የሚጠይቁ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል። 157 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎባቸው የተመረቁ መሠረተ ልማቶች በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ መሠረተ ልማቶችን እድገት የሚያሳዩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። በከተማዋ በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች እየተመለሱ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። የሕዝብ ቤተ መጻሕፍትን፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ የመንገድ ዳር መብራቶችን በመሥራት ጥያቄዎችን እየመለሱ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ዛሬ የተመረቁት መሠረተ ልማቶችም በዓለም ባንክ፣ በኅብረተሰቡና በከተማ አሥተዳደሩ የተገነቡ መኾናቸውን ነው የገለጹት። የከተማዋ ሕዝብ ለልማት ቀናዒ መኾኑን ያነሱት ከንቲባው ላደረገላቸውና ለሚያደርግልቸው ድጋፍ ኹሉ አመሰግነዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መልካሙ ተሾመ ከተሜነት የሚገለጸው በሕዝብ ስብስብ ሳይኾን በልማትና በአኗኗር ዘይቤ ነው ብለዋል። ከተሞቻችን በማይመጥናቸው የመሠረተ ልማት ችግሮች ውስጥ ቆይተዋል ነው ያሉት አሥተዳዳሪው ከተሞችን የሚመጥን ሥራ ለመሥራት የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል። ዛሬ የተመረቁት መሠረተ ልማቶች የነዋሪዎችን ሕይወት ቀላል የሚያደርጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል። መሠረተ ልማቶች ተሰርተው እንዲጠናቀቁ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አሰፋ ሲሳይ 680 ከተሞችን እያስተባበሩ ከተሞቹ ለነዋሪዎች ምቹና ጽዱ እንዲኾኑ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የገለጹት። ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። በከተማዎቹ የቤት አቅርቦት በትኩረት እየተሠራበት መኾኑንም አንስተዋል። የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን እንዲፈቱ ከተሞች ገቢያቸውን በአግባቡ መሰብሰብ ፣ ሕዝቡም ለመሠረተ ልማት ድጋፍ ማድረግ አለበት ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) ተዋናዮቹ የተለያዩ ይሁኑ እንጂ የሠራነው ሥራ አንድ ነው ብለዋል።የተመረቁት መሠረተ ልማቶች ሕዝብን የሚያገለግሉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ሕዝብን ለማገልገል የሥራ ድንበር የለውም ብለዋል። የተቀናጀን ሀብት እና መልካም የመተሳሰብ ባሕልን ይዘን ልማት እንሠራለን ነው ያሉት። የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን ጠብቆ ማቆዬት ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። በሚቀጥሉት ዓመታት ሌሎች ልማቶችን መሥራት አለብን ነው ያሉት። በተመሳሳይ የልማት አጀንዳ በአንድነት መሥራት አለብንም ብለዋል።

የንግድና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ዴዔታ እንዳለው መኮንን፣ ኢትዮጵያ እምቅ ሀብት ያላት ብትኾንም የተሠራው ሥራ በቂ ባለመኾኑ አብዛኛው ሕዝብ በችግር ቆይቷል ነው ያሉት። መንግሥት ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የልማት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። ፍላጎታችን ሰፊ፣ መንገዳችን ረጅም ነውም ብለዋል። ከተባበርን ወደ ምንፈልገው ከፍታ ማደግ እንችላለንም ብለዋል። እይታችንን ከተረጅነት አውጥተን በሥራ መለወጥ ላይ ማተኮር አለብንም ብለዋል ሚኒስቴር ዴዔታው። የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት ለተባበሩ ባለሀብቶችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እንደ ሕዝብ ለመጽናት እንደሀገር ለመኖር የዉስጥ ሰላም የወል ሀሳባችን እና የጋራ መግባቢያችን ሊሆን ይገባል” የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
Next articleበኩር ጋዜጣ በሐምሌ 24/2015 ዓ.ም ዕትም