
ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር ማለት የሰዉ ልጆች ማኀበራዊ ስሪት ነዉ። ይህ ማኀበራዊ መስተጋብር በዜጎች መካከል በሚፈጠር ተፈጥሯዊም ሆነ ሰዉ ሠራሽ ልዩነት ዉስጥ በሚፈጠር የተቃርኖ ስንጥቅ የሚሰፋዉ እና የሚደፈርሰዉ በሰላም እጦት ነዉ። ይህ ሁኔታ ሰላም የሰዉ ልጆች የእለት ከእለት ኑሮ ዉስጥ በአጽንዖት ከሚፈልጉት አንኳር ጉዳይ አንደኛዉና ብቸኛዉ መፍትሔ መሆኑን ያስረዳናል።
በዘልማድ ሰላም ከዉስጥ የሚመነጭ መሆኑን ባለመረዳት አንዳንዶቻችን አንጋጠን ሰላምን ከኛ ዉጭ እንናፍቃለን። አለፍ ሲልም ሀሳብን ወደ ጠረጴዛ ከማምጣት ይልቅ ወደ አክሳሪ እና ከፋፋይ ግጭት እንወስደዋለን። ያኔ የሰላም አየር ከባለቤቱ ይርቃል፤ አብሮነት ይናጋል፤ አንድነት ይኮሰምናል።
ሰላም በናፍቆት ወይም በመሻት አይመጣም ይልቅ ከራስ የሚጀምር አልፎም ለሌሎች የሚተርፍ ሰዋዊ እሳቤ ነዉ። በግርግር ወይም በብጥብጥ ዉስጥ ሰላምን መፈለግ ደመናን እንደመጨለፍ ይቆጠራል።
በልዩነት እና በግጭት የሚገኝ ሰላም፣ የሚጸና አንድነት እና የሚቆም ሀገር የለም። የሚመለስ የክልሉ ሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄም አይኖርም። ፍላጎቶቻችንና ጥያቄዎቻችን ሁሉ የሚመለሱት በሰላማዊ ትግልና በሰላም ብቻ ነው።
እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ የከረሩ ልዩነቶችን ምክንያት አድርጎ እየጎላ የመጣዉ መጠራጠር እና አለመተማመን ሰላምን የሩቅ ሀገር አድርጎብናል። የዚህ ፈተና እያደገ መምጣት ደግሞ ሰላምን ከራስ የሚመነጭ ሳይሆን ከሌሎች የሚቸረን አድርገን በማሰባችን ነዉ።
እንደ ሕዝብ አንድ ሆኖ ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ልማት ለማምጣት ከዉስጥ የጀመረ ሰላም ብቸኛዉ ጋሻ ነዉ። ሰላም ሲኖር አንድነት፣ ፍቅር፣ ደስታ፣ እድገትና ልማት ተከታትለዉ ይመጣሉ።
የተለያዬ አሰላለፍ ውስጥ የገባ ማኅበረሰብ ወይም ሕዝብ የተሰናኘ የሕዝብ አቅም ኑሮት ችግሮችን በአሸናፊነት መሻገር እንደማይችል የምንረዳበት ጊዜዉ አሁን ነዉ።
ስለሆነም እንደ ሕዝብ ለመጽናት እንደሀገር ለመኖር ሰላም የወል ሀሳባችን እና የጋራ ቋንቋችን ሊሆን እንደሚገባ በመገንዘብ ለሰላም እና ለዉይይት በራችን ክፍት አድርገን ለጋራ ሰላማችን ዘብ በመሆን እንድ ሆነን በአንድ በመቆም በጋራ መሥራት ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን ልንረዳ ይገባል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!