“መጻዒ እጣ ፋንታችን የሚወሰነው በሌሎች ይኹንታ ሳይኾን በራሳችን አቅም ነው” አቶ አታላይ ታፈረ

92

ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ተፈጥሯዊ የኾነውን የተከዜ ወንዝ ድንበር ጥሰው ወረራ የፈጸሙት ጠባብ ብሔርተኞች ህወሃት በአማራ ሕዝብ ላይ ዘርፈ ብዙ ብዝበዛዎችን ፈጽመዋል። ወያኔ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ በተሻገረው የጭቆናና የምዝበራ ዘመኑ በአማራ ሕዝብ ላይ ያደረሰው ግፍ እና መከራ የትውልድ ክፍተት የፈጠረ ክስተት ተደርጎ ይወሰዳል።

አማራ ነን በማለታቸው ብቻ በወያኔ ኃይሎች የተገፉት፣ የተገረፉት፣ የተሰደዱት እና የተገደሉት ብዙዎች ናቸው። የወያኔ ግፍ ያላቆረቆዘው ቤተሰብ እና ያላዳከመው ማኀበረሰብ የለም። አሁን ላይ ጀግኖቹ ቀን ጠብቀው ማንነታቸውን በእጃቸው አስገብተዋል።

ዛሬ ከነጻነት ማግስት ጀምሮ ተፈጥሯዊ መብታችን የኾነውን መንግሥታዊ በጀት በተለያዩ ምክንያቶች አላገኘንም የሚሉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በሕዝብ ተሳትፎ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ግን ጀምረው እያጠናቀቁ ነው።

በጀት ነጻነትን አይተካም የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች በአንድ እጃችን ነጻነታችን እናጸናለን፤ በሌላ እጃችን ደግሞ በራሳችን አቅም መልማታችን አናቆምም ነው ያሉት።

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ቃብትያ ወረዳ በአዲ ኽርዲ ከተማ በሕዝብ ተሳትፎ የተገነቡ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተጠናቅቀው ለአገልገግሎት ክፍት ኾነዋል። የቃብትያ ወረዳ አሥተዳዳሪ አታላይ ታፈረ በምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንዳሉት የወልቃይት ሕዝብ የትኛውንም አይነት ፈተና ለመሸከም አቅም እንዳለው አሳይቷል።

ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በወያኔ ጨቋኝ ሥርዓት እልፍ አዕላፍ ግፍ እና በደል ተፈጽሟል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ኾን ተብሎ የተሰራጨው የተሳሳተ ትርክት እስከ ቅርብ ጊዜያትም ዋጋ የሚያስከፍል እኩይ ሴራ ነበር ብለዋል።

“ከፋኝ” ብለው ተደራጅተው በዱር በገደሉ መሥዋዕትነት የከፈሉት ቀደምቶቻችን ድካማቸው ከንቱ አልቀረም ለዛሬዋ ነጻነት አብቅቶናል ነው ያሉት። የተገኘውን ነጻነት ለማጽናት እና ለማስቀጠል የአሁኑ ትውልድ ለአፍታ እንኳን ሳይዘናጋ ያስቀጥላል ብለዋል።

በመራር ትግል እና መሥዋዕትነት የተገኘውን ነጻነት ዛሬም እንደትናንቱ በሐሰት ፕሮፖጋንዳ እቅዳችን ይሳካል ብለው የሚሞክሩ አይታጡም ያሉት አቶ አታላይ “መጻዒ እጣ ፋንታችን የሚወሰነው በሌሎች ይኹንታ ሳይኾን በራሳችን አቅም ነው” ብለዋል። መንግሥታዊ በጀት በሌለበት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ማጠናቀቅ ለየትኛውም አይነት መሥዋዕትነት ዝግጁ መኾናችን ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ ደረጃውን የጠበቀ የሕዝብ ቤተ መጽሐፍት በአንድ ግለሰብ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል። ሦስት አምቡላንሶች ውጭ በሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ተገዝተው ተበርክቷል ያሉት አቶ አታላይ ሕዝቡም በጦርነት ቢጎዳም ለራሱ ልማት ግንባር ቀደም ባለቤት በመኾን ተሳትፎ አድርጓል ብለዋል።

የውስጥ ለውስጥ ጠጠር መንገድ፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የውኃ መስመር ጥገና እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ሥራዎች ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ ኾነዋል ተብሏል።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article30 ሚሊዮን በሚጠጋ ወጪ የተገነባው የናኒና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።
Next article“እንደ ሕዝብ ለመጽናት እንደሀገር ለመኖር የዉስጥ ሰላም የወል ሀሳባችን እና የጋራ መግባቢያችን ሊሆን ይገባል” የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ