
ሁመራ : ሐምሌ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እርግጥ ነው ከ1970ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ሕይዎት እንደ አጋጣሚ በዚህ አካባቢ የጣለቻቸው ህጻናት እድለኞች የሚባሉ አልነበሩም፡፡ ታላላቅ ወንድሞቻቸው በጠባብ ብሔርተኞች እየታደኑ ተለቅመዋል፡፡ አባቶቻቸው አዲስ ማንነት አንቀበልም በማለት “ከፋኝ” በሚል የትግል ስም ተደራጅተው ውሏቸው በገደል፣ አደራቸው በዱር ተወስኖ ነበር፡፡ አማራ ነን ያሉ ተማሪዎች በአቻዎቻቸው ፊት አደባባይ ላይ ቆመው እንዲሸማቀቁ ተደርገዋል፡፡
ለግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት እና ራያ አማራዎች ወልዶ መሳም አሽቶ መቃም ተከልክለው፤ ከርስታቸው እና ከጉልታቸው ተነቅለው ውጣ ውረድ የበዛባቸውን የትግል ጊዜያት አሳልፈዋል፡፡ በእነዚህ አካባቢ በአማራ ሕዝብ ላይ አስከፊ የዘር ጭፍጨፋ፣ አሳፋሪ የታሪክ ሽሚያ እና አስደንጋጭ የባሕል ወረራ ተስተውሏል፡፡ የፖለቲካ ሴራ እሳት ኾኖ የበላቸው ወጣቶች ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡ ታሪክ አዋቂዎች እና እውነት ተናጋሪዎች ዱካቸው እየተፈለገ እንደ እሾክ ተመንጥረዋል፡፡
አማራ ነን ያሉ ወጣቶች የሃሰት ታርጋ እየተለጠፈባቸው ታፍነው ተወስደው የደረሱበት አልታወቀም፡፡ ባሕላችን ጎንደር፤ ቋንቋችን አማርኛ ፤ድንበራችን ተከዜ ምላሽ ያሉ መኳንንት እና መሳፍንት እርስታቸው ተነጥቆ እና ሀብታቸው በቁም አልቆ አንገት ደፍተው እንዲኖሩ ተገድደዋል፡፡ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው የወልቃይት ጠገዴ ተቆርቋሪዎች በእልህ እና ቁጭት ሲብሰለሰሉ ኖረው ወደ ማይቀርበት ዓለም አልፈዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ሲያወሩ ዛሬም ድረስ የደረሱበት ያልታወቁት እና ደብዛቸው የጠፋ እጅግ በርካታ ናቸው ይላሉ፡፡
በዚህ ሁሉ መካከል ደግሞ ውስኖች አንገታቸውን ደፍተው ቀን እየጠበቁ በፈጣሪ ተዓምር እድሜ ተሰጥቷቸው ያንን አስከፊ ዘመን እንደ ታሪክ ይመሰክሩ ዘንድ “ለወሬ ነጋሪ” ብቻ ቀርተዋል፡፡ ክፉና ደጉን፤ ወጪና ወራጁን እያስተዋሉ እንደ ነፍሰ ጡር የጭንቅ ቀናትን እየቆጠሩ አሳልፈዋል፡፡ በድንበር አካባቢ የነበሩት እድለኞች ባሕር አቋርጠው እና ድንበር ተሻግረው በባዕድ ሀገር ግዞተኞች እና ስደተኞች እየተባሉ አሳልፈዋል፡፡ ነገር ግን ትውልድ እንደ ጅረት ነው፤ ገባር ሲያገኝ ይገነባል፡፡ አንዱ አልፎ ሌላው ሲተካ ከአባት የወረሰውን ልጅ ያስቀጥላል፤ ለልጅ ልጆቹም ያስረክባል፡፡
ዛሬ ላይ የወያኔ ዘመን የግፍ አገዛዝ አልፎ በኃይል የተወሰዱ አካባቢዎች ወደ ቀደመ ቦታቸው ተመልሰዋል፡፡ ነጻ ከወጡ አካባቢዎች መካከል ቃብትያ ሁመራ ወረዳ አንዷ ነች፡፡ ምንም እንኳን ቃብትያዎች ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ባሳለፉት የግፍ አገዛዝ ምክንያት ጎደሎዎቻቸው የበዙ ቢኾኑም ለመልሶ ግንባታው የሚደረገው ድጋፍ የበርካቶችን ቀልብ የሚገዛ ነው ይላሉ ነዋሪዎቹ፡፡ በውጭ ሀገራት የሚኖሩት የአካባቢው ተወላጆች የወረዳዋን ክፍተት በሚገባ ያውቃሉና ድጋፎቻቸው ሁሉ የተጠኑና የተደራጁ ናቸው፡፡
ትውልድ እንደ ጅረት በሚንሰላሰልባት ኢትዮጵያ ከትናንቱ መማር የሚቻለው ተተኪ ትውልድ ሲገነባ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ትናንት በአዲ ኽርዲ እንኳንስ የሕዝብ ቤተ መጽሐፍት ቀርቶ ትምህርት ቤቶች እንኳን የተሟላ ግብዓት አልነበራቸውም የሚሉት ቃብትያዎች ከነጻነት ማግስት በውስጥም በውጭም የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች የጎደለውን ለመሙላት የጠፋውን ለመተካት ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ቃብትያን እና አካባቢውን መልሶ ለመገንባት ከተደረጉ ጥረቶች መካከል “የዘነበ ማሩ መታሰቢያ ቤተ መጽሐፍት” ግንባታ አንዱ ነው፡፡
ነሐሴ 8 ቀን 1986 ዓ.ም በአሜሪካ ኮሎምበስ ተወልዶ የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም ይህችን ዓለም ገና በወጣትነቱ የተለያት ዘነበ ማሩ ወላጆቹ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ አባቱ አቶ ማሩ አምዶም ካሳ እና እናቱ ወይዘሮ ኤልሳ አስራጋው ትውልድ እና እድገታቸው በዚሁ አካባቢ እንደኾነ ይነገራል፡፡ በሀገረ አሜሪካ የሚኖሩት እነኝህ ወልቃይቴዎች ከነጻነት ማግስት አካባቢውን መልሰው ለመገንባት እጃቸውን ከዘረጉት እልፎች መካከል በአካባቢው ማኀበረሰብ ዘንድ ቀድመው ይጠቀሳሉ፡፡
ከታሪካዊቷ የእምብርት ተራራ ግርጌ፤ ከተማሩበት ትምህርት ቤት ራስጌ ላይ ማዘጋጃ ቤት የሰጣቸውን ቦታ ትውልድ ይቀረጽበት ዘንድ ቤተ መጽሐፍት ገነቡበት፡፡ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበት የተገነባው ቤተ መጽሐፍት ለዚህ ዘመን እድለኛ ትውልድ የዓይን ማረፊያ ኾኗል፡፡
“ዘነበ ማሩ መታሰቢያ ቤተ መጽሐፍት” ለሌሎች የልማት አርበኞች እንደ ሞዴል የቀረበ ትርሩፋት ነው፡፡ ዛሬ ከትምህርት ሰዓት ውጭ ተማሪዎች ደረጃውን በጠበቀው እና ከትምህርት ቤታቸው አቅራቢያ በተገነባው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ትርፍ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡
ትናንት ያንን ሁሉ የመከራ እና የጨለማ ዘመን ያሳለፍነው በማንነታችን ነበር የሚሉት የአዲ ኽርዲ መሪ ማዘጋጃ ቤት ሹም አቶ ደጀን ለማ ያሳለፍነው ጊዜ እንዳይደገም ትውልድ ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ህጻናት እና ወጣቶች አማራ ነን እያሉ እና አማራ በመኾናቸው ብቻ በርካታ የሥነ ልቦና ጫና ደርሶባቸዋል የሚሉት አቶ ደጀን የተሰበረውን የትውልድ ሥነ ልቦና ለመጠገን በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፎ የላቀ ነው ብለዋል፡፡ በውጭ የሚኖሩት ተወላጆች በአካባቢው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እስከመገንባት የደረሰ ዕቅድ እና እንቅስቃሴ እንዳላቸውም ገልጸውልኛል፡፡
ዞኑ የመንግሥት በጀት ሳይመደብለት ላለፉት ሦስት ዓመታት ነጻነቱን ብቻ ተስፋ አድርጎ ቆይቷል የሚሉት አቶ ደጀን በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ድጋፍ ተኪ የለውም ነበር ብለዋል፡፡ከትውልድ ቀያቸው በግፍ ተሰድደው በውጭ ሀገር ኑሯቸውን መምራት ከጀመሩ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም “ትንሽ ሥጋ እንደ መርፌ ትወጋ” ነውና ከነጻነት ማግስት አካባቢያቸውን መልሶ ለመገንባት የቀደማቸው አልነበረም ብለውኛል፡፡ ከነጻነት ማግስት ከሁሉ ነገር ቀድሞ ሦስት አምቡላንሶችን ገዝተው ሰጥተዋል፡፡
ምንም እንኳን ሕዝቡ በመንግሥት የተበጀተ በጀት ባይኖረውም፤ በርካታ ጊዜያትን በጦርነት ውስጥ ቢያሳልፍም በራሱ ልጆች መመራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን በትኩረት እየሠራ ነው፡፡ ከ22 ሚሊዮን በላይ ብር ከሕዝብ በማዋጣት በበጋ አቧራ በክረምት ደግሞ ጭቃ የምትለብሰውን ከተማ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ሠርተው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
ዛሬ ከክልል፣ ከዞን እና ከአጎራባች አካባቢዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበትም የመሠረተ ልማት ግንባታ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ይካሄዳል፡፡ ነዋሪዎቹም ኑ ለዘመናት የተፈጠረውን የትውልድ ክፍተት በጋራ እንሙላ! ብለዋችኋል።
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!